ከዓለም ህዝብ 5 ቢሊየኑ የሞባይል ኔትዎርክ ተጠቃሚ ሆኗል- ሪፖርት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከዓለም ህዝብ ውስጥ ሁለት ሶስተኛው ወይም 5 ቢሊየኑ የሞባይል ኔትዎርክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኑን አንድ ሪፖርት አመላክቷል።

ጅ.ኤስ.ኤም.ኤ የተሰኘ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሰረት በቀጣይ ዓመታት የሞባይል ኔትዎርክ ተደራሽነት በምን ሁኔታ ሊቀጥል እንደሚችልም ትንበያውን አስቀምጧል።

ሪፖርቱ በሳንፍራንሲስኮ በተካሄደው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የሞባይል ኮንግረስ ስብሰባ ላይ የቀረበ ሲሆን፥ የሞባይል ተጠቃሚው ህዝብ ቁጥር በጣም ብዙ ቢሆንም እድገቱ ግን አዝጋሚ ነው ተብሏል።

የተጠቃሚዎቹ ቁጥር ከ4 ቢሊየን ወደ 5 ቢሊየን ለመሸጋገርም አራት ዓመታት ጊዜ ወስዶበታል ነው ያለው ሪፖርቱ።

በቀጣይም ቀሪውን ህዝብ በሞባይል ለማስተሳሰር የሚደረገው ጉዞ በርካታ ዓመታትን ሊወስድ እንደሚችል ትንብያ ተቀመጧል።

የስማርት ስልኮችና የሞባይል ብሮድባንድ ተጠቃሚዎች ቁጥር ማደግ ደግሞ የኢንተርኔት ትስስሩን እና አጠቃቀሙን ቢያሳድገውም ሌላ ጫና ይዞ መጥቷል።

የኢንተርኔት ኢንዱስትሪው ከአራተኛ ትውልድ አልፎ ወደ አምስተኛ ትውልድ ቢገባም የአራተኛ ትውልድ ኔትወርክ ተጠቃሚው ቁጥር ጥቂት ነው።

በፈረንጆቹ 2025 የዓለም የሞባይል ኔትወርክ አሁን ካለው የአራተኛ ትውልድ ተጠቃሚ ብዛት በአንድ አራተኛ ብቻ እንደሚጨምር ይገመታል።

ይህ እድገት የሚመዘገበውም በአሁኑ ወቅት ብራዚል፣ ህንድ እና ኢንዶኔዥያ የአራተኛ ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎታቸውን ለማስፋት የሚያደርጉትን ጥረት ታሳቢ በማድረግ ነው።

በቀጣይ ከአራተኛ ትውልድ ወደ አምስተኛ ትውልድ የኔትወርክ ስርጭት ለማሸጋገር ያልተማከለ የአገልግሎት ስርዓትን መዘርጋት፣ ቀላል መንገዶችን መምረጥና የአቅራቢያ የኔትወርክ ቀጠናዎችን በመምረጥ ሊያጋጥም የሚችለውን እንቅፋት መቀነስ እንደሚቻል ተነግሯል።

የኔትወርክ ሽግግርን በሶፍትዌር እንዲታገዝና ተጠቃሚዎች በቀላሉ ሊቀይሩት የሚችሉት ከስልኮች ጋር የሚናበብ መሆኑም ተመራጭ ነው።

በዚህ ወቅት ፌስቡክ፣ አማዞን፣ አፕል፣ ኔትፈሊክስ እና ጎግል ኩባንያዎች የኔትወርክ አቅሙ የሚመጥነውን ከፍተኛ የቴሌኮም ኦፕሬተር እድገት ከ2010 ጀምሮ በማስመዝገብ ለኔትወርክ አጠቃወም ባህሉ መዳበር ሚናቸው የጎላ መሆኑ ተጠቀሷል።

ምንጭ፦ሲ ጅ ቲ ኤን