ኤቲ ኤንድ ቲ ገመድ አልባ የ5G ኔትዎርክን በዚህ ዓመት ስራ ላይ እንደሚያውል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተለያዩ የቴሌኮም ኩባንያዎች በመሞከር ላይ የሚገኙት ፈጣኑ የ5G ኔትዎርክ እውን የመሆኑ ነገር የተቃረበ ይመስላል።

ኤቲ ኤንድ ቲ የተባለው የአሜሪካ የቴሌኮም ኩባንያ ገመድ አልባ የ5G ኔትዎርክን በዚህ ዓመት ለተጠቃሚዎች ማቅረብ እንደሚጀምር አስታውቋል።

ኩባንያው የዓለማችን ፈጣኑ የሆነውን የ5G ኔትዎርክ በአዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት 2018 አጋማሽ ላይ ማቅረብ እንደሚጀምርም ተነግሯል።

ኩባንያው ገመድ አልባ የ5G ኔትዎርኩን በመጀመሪያ ዙር በ12 የአሜሪካ ከተሞች ማቅረብ እንደሚጀምር ያስታወቀ ሲሆን፥ የከተሞቹን ዝርዝር ግን አላስታወቀም ነው የተባለው።

5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትዎርክ (5G) በመባል የሚጠራው ኔትዎርክ ከሞባይል ኔትዎርክነቱ ባሻገር የተለያዩ ጥራት ያላቸውን ቪዲዮች ከማስተላለፍ እስከ አሽከርካሪ አልባ መኪናዎች ድረስ ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል።

የዓለማችን ታላላቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በ5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትዎርክ (5G) ላይ የተለያ ሙከራዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው ሳምሰንግ የ5G ኔትዎርክን በጃፓን ፈጣን ተንቀሳቃሽ ባቡር ላይ ስኬታማ ሙከራ ማካሄዱን ይታወሳል።

በባቡሩ በተገጠመው የ5G ኔትወርክ በተደረገ ሙከራም 1 ነጥብ 7 ጊጋ ባይት መረጃ በሰከንድ መላክ መቻሉ እና የግንኙነት ሁኔታ በስኬት መሞከሩ ተነግሯል።

ኤሪክሰን የተባለው ኩባንያ ደግሞ የዓለማችን ፈጣኑ የተባለውን የ5G ኔትዎርክ በህንድ የሞከረ ሲሆን፥ ሙከራውም በሰከንድ የ5 ነጥብ 7 ጊጋ ባይት መረጃ የማስተላለፍ ፍጥነት እንደነበረው ታውቋል።

የኳል ኮም ኩባንያም በ5ኛው ትውልድ (5G) ኔትዎርክ የሚሰራ ስማርት ስልክ መስራቱም ይታወሳል።

ምንጭ፦ www.bloomberg.com