ኤች.ፒ ከ50 ሺህ በላይ የኮምፒውተር ባትሪዎችን ከዓለም ዙሪያ ተሰብስበው እንዲመለሱ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ግዙፉ የኮምፒውተር አምራች ኤች.ፒ በዓለም ዙሪያ ለሽያጭ ተለቀው የነበሩ ከ50 ሺህ በላይ የኮምፒውተር ባትሪዎች ከገበያ ላይ ተሰብሰብው ወደ ፋብሪካው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።

ከዓለም ገበያ ላይ ተመልሰው እንዲሰበሰቡ ጥሪ የቀረበባቸውም ለኤች.ፒ ኖት ቡክ ኮምፒውተር እና ሞባይል ዎርክ ስቴሽን ጥቅም ላይ የሚውሉት የሊትየም አየን ባትሪዎች መሆኑም ተነግሯል።

ኩባንያው 8 ደንበኞቹ የኮምፒውተር ባትሪው ላይ ከመጠን በላይ መጋል፣ መቅለጥ እና የመጨስ ምልክቶችን እንዳዩ ሪፖርት ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው ባትሪዎቹ እንዲመለሱ ጥሪ ያቀረበው ተብሏል።

“የኤች.ፒ ምርቶች ጥራት እና ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኤች.ፒ ኖት ቡክ ኮምፒውተር እና ሞባይል ዎርክ ስቴሽን ባትሪዎች ላይ ችግር እንዳለው መረጃ ደርሶናል ብሏል” ኩባንያው በብሎግ ፖስት ገፁ ላይ።

“በችግሩ ላይ አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ እየሰራን ነው ያለው ኩባንያው፤ ፍቃደኛ የሆኑ ሰዎችም ባትሪዎቻቸውን መልሰው በአዲስ አንዲተካላቸው ማድረግ ይችላሉ” ብሏል።

ባትሪያቸው ላይ ችግር አለባቸው የተባሉት የኤች.ፒ ፕሮቡክ ኮምፒውተሮች ናቸው የተባለ ሲሆን፥ እነዚህም

የኤች.ፒ ፕሮቡክ 64x G2 እና G3፣ 65x G2 እና G3

ኤች.ፒ x360 310 G2፣ ኢ ኤን ቪ ዋይ m6

ኤች ፒ ፓቪሊየን x360፣ ኤች.ፒ 11 ኖትቡክ

ኤች.ፒ ዜድ ቡክ 17 G3፣ 17 G4 እና ስቱዲዮ G3 ናቸው

በተጨማሪም ደንበኞች የሚጠቀሙት ኮምፒውተር ባትሪ በኩባንያው ድረ ገፅ www.HP.com/go/batteryprogram2018 በመግባት ለአደጋ የተጋለጠ አሊያም ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ማየት ይችላሉ ተብሏል።

ምንጭ፦ www.techworm.net