ትዊተር የሩብ አመት የመጀመሪያ ትርፍ ማስመዝገቡን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ትዊተር በማህበራዊ የትስስር ገፁ ላይ የቪድዮ ማስታወቂያ ሽያጭ በመጨመሩ ምክንያት በመጀመሪያው ሩብ አመት ትርፋማ መሆኑን የሚያሳይ ሪፖርት አውጥቷል።

በዚህም ምክንያት በአክሲዮን ገበያ የኩባንያው የድርሻ ዋጋ በ12 በመቶ ማደጉ ተገልጿል።

ይህ ሁሉ የሆነው የማህብራዊ ትስስር ገፁን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ከተጠበቀው በታች በሆነበት ወቅት ነው ተብሏል።

የትዊተር ወራሀዊ የተጠቃሚዎች ቁጥር በ4 በመቶ አድጎ 330 ሚሊየን ቢደርስም፥ በዩናይትድ ስቴትስ ግን የተጠቃሚዎቹ ቁጥር ከ69 ሚሊየን ወደ 68 ሚሊየን ወርዷል።

በፈረንጆቹ 2016 አራተኛ ሩብ ዓመት 167 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ኪሳራ ያጋጠመው ትዊተር፥ በ2017 በተመሳሳይ ወቅት 91 ነጥብ 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱ ነው የተነገረው።

በዚህም በ2018 ትርፋማ ሆኜ አሳልፋለሁ ብሏል ኩባንያው።

ትዊተር ከቪዲዮ ጋር ተያይዞ በማህብራዊ ትስስር ገፁ ላይ ያደረገው ማሻሻያ ለስኬቱ ምክንያት መሆኑም ተመልክቷል።

 

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ