የጎግል አዲስ ምርት የሆነው ፒክስል 3 የስማርት ስልክ ሙሉ ዝርዝር አፈትልኮ መውጣቱ ተሰምቷል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጎግል አዲስ ስማርት ስልክ ምርት የሆነው ፒክስል 3 ሙሉ ዝርዝር መረጃ አፈትልኮ መውጣቱ ተነግሯል።

የጎግል ፒክስል 3 ስማርት ስልክ ዝርዝር መረጃው ከሩሲያዊ ብሎገር የቴሌግራም አድራሻ ላይ የተገኘ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅትም በርከት ያሉ ድረ ገፆች እየተቀባበሉት ይገኛሉ።

አፈትልኮ ወጣ የተባለው መረጃ ላይ የስማርት ስልኩ ፎቶ ግራፍ ባይወጣም፤ ሌሎች ዘርዘር ያሉ ነገሮች መታወቃቸው ነው የተነገረው።

በዚህም በምርት ሂደት ላይ ያለው አዲሱ የጎግል ፒክስር 3 ስማርት ስልክ በአሁኑ ወቅት በገበያ ላይ ካሉ ምርቶቹም ይሁን ከአይፎን X በጣም የቀጠነ (ጠፍጣፋ) መሆኑ ነው የተነገረው።

ከዚህ በተጨማሪም ለጆሮ ማዳመጫ (ሄድ ፎን) መሰኪያው ከመደበኛው በተጨማሪ ከዩ ኤስ ቢ ጋር የሚመሳሰል መሰኪያ ማዘጋጀቱም ነው የተነገረው።

እንዲሁም የጎግል ፒክስል 3 ስማርት ስልክ ስክሪን ጥራትም 2960×1440 ፒክስል ሲሆን፥ አሁን በገበያ ላይ ካለው ፒክስል 2 ጥራቱ በጣም የተሻለ ነው ተብሏል።

እንዲሁም 4 ጊጋ ባይት ራም እና 845 SoC ፕሮሰሰር የሚገጠምለት መሆኑንም አፈትልኮ የወጣው መረጃ አመልክቷል።

ምንጭ፦ fossbytes.com