ስር የሰደደ የድካም ስሜት ወይም የሰውነት መዛልን ለማሰወገድ…

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የድካም ስሜት አብዛኛውን ጊዜ በተደራራቢ ስራ፣ በጤና መታወክ እና በተዛባ እንቅልፍ ምክንያት ሊያጋጥመን ይችላል።

ከድካም ጋር ተያይዞ የሚመጣው ስር የሰደደ የድካም ስሜት አብዛኛውን ጊዜ ከወንዶች ይልቅ ሴቶችን ሊያጠቃ እንደሚችልም ጥናቶች ይናገራሉ።

ይህ ስር የሰደደ የድካም ስሜት የሚጋጥማቸው ሰዎችም የሰውነታቸው በሽታ የመከላከል አቅም እንዲቀንስ የሚያደርግ ሲሆን፥ በቀላሉ ለድብርት ሊጋለጡ ይችላሉም ተብሏል።

ለስራችን የምንሰጠውን ትኩረት መቀነስ፣ የጉሮሮ፣ የጡንቻ፣ የመገጣጠሚያ አካላት ህመም እንዲሁም እንቅልፍ የማጣት ችግር እና የራስ ምታት የመሰሳሰሉ ስሜቶች የሚሰሙን ከሆነም ስር የሰደደ የድካም ስሜት የፈጠረብን ችግር ነው ሲሉም ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

ድብርት፣ ያልሰትስተካከለ አመጋገብ፣ የተዛባ እንቅልፍ፣ እንደ ካንሰር፣ ስኳር በሽታ፣ የልብ ህመም፣ አልኮል አብዝቶ መውሰድ፣ ከህመም እና ከመድሃኒቶች ጋር ተያየዘው የሚመጡ ኢንፌክሽኖች እንዲሁም ከመተንፈሻ አካላት ጋር ተያየዘው የሚመጡ እንደ አስም፣ ብሮንካይት አይነት ህመሞች ሊዚህ ችግር መንስዔ ናቸው ተብሏል።

የድካም ስሜትን ለማሰወገድ ምን ማድረግ ያለብን

ራሳችንን ማረጋጋት፦ ውስጣቸንን ሊያረጋጉን የሚችሉ ሙዚቃዎችን ማዳመጥ፣ ውስጣቸን ሰላም እንዲሰማን የሚያደርጉ የጸሎት ቃላትን ደጋግሞ ማለት፣ እራሳችንን በምናብ ደስ ወደሚሉ ቦታዎች ላይ እንዳለን አድርገን በማሰብ እራሳችንን ማረጋጋት እንችላለን ተብሏል።

ጊዜያችንን በአግባቡ መጠቀም፦ ከእንቅልፋችን በጊዜ በመንቃት በቀን ውስጥ ማከናወን ያለብንን ካቀድን በኋላ በእቅዳቸን መሰረት ያለንን ጊዜ በአግባቡ መጠቀምም የጭንቀት ስሜት እንዳይሰማን በማድረግ ሰውነታችንን ስር ከሰደደ የድካም ችግር መከላከል እንችላለን።

አመጋገባችንን ማስተካከል፦ ምግብ አለመመገብ ስር የሰደደ የድካም ስሜት እንዲሰማን ስለሚያደርግ በተቻለን አቅም በየጊዜው ምግበም መመገብ ይመከራል።

በተጨማሪም የድካም ስሜት እንዲሰማን ሊያደርጉ የሚችሉ ስብ የበዛባቸውን ምግቦችን ከመመገብ መቆጠብም ይረዳናል ተብሏል።

የምንወስደውን የአልኮል መጠን መቀነስ፦ አልኮል በተፈጠሮው የድካም ስሜት እንዲጫጫነን ስለሚያደርግ በተቻለን አቅም አልኮል ከመጠጣት መቆጠብ ካልሆነም መጠኑን መቀነስ ጠቃሚ ነው።

አሌከትሮኒክስ እቃዎች ጋር ያለንን የቆይታ ጊዜ መቀነስ፦ እንደ ስማርት ስልኮች፣ ቴሌቭዥን፣ ኮምፒውተር እና ሌሎች የኤሌክሮኒክስ ምርቶች ላይ አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናሳልፍ ከሆነ በቀላሉ ለድካም ስሜት እንድንጋለጥ ስለሚያደርገን ከነዚህ ቁሶች ጋር ያለንን የቆይታ ጊዜ መቀነስ የሚመከር ሲሆን፥ በተለይም በመኝታ ሰዓት በተቻለን አቅም ከአካባቢያችን ማራቅ ጥሩ ነው።

በቂ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ፦ በቀን ውስጥ ለ30 ደቂቃ ያከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማደረግ ስር የሰደደ የድካም ስሜትን ለመከላከል ፍቱን ነውም ተብሏል።

በቂ እንቅልፍ መተኛት፦ ስር የሰደደ የድካም ስሜት እንዳያጋጥመን በቀን ውስጥ ቢያንስ ከ6 እስከ 8 ሰዓት መተኛትንም ተመራማሪዎቹ ይመክራሉ።

እነዚህም ዘዴዎች ተጠቅመን ስር ከሰደደ የድካም ስሜት እራሳችንን መፈወስ ካልቻለን ወደ ጤና ተቅሟት በመሄድ ሀኪም ማማከር እንዳለብንም ተመራራሪዎቹ ይመክራሉ።

ምንጭ፦ wellnessbin.com

በድጋሚ የተጫነ