ሁለት የተመድ ድርጅቶች ከአካባቢ ብክለት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና ችግሮችን ተባብረው ለመከላከል ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም እና የዓለም ጤና ድርጅት ከአካባቢ ብክለት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና ችግሮችን በጋራ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።

እነዚህ ከአካባቢ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና ቸግሮች በዓለም ላይ በየዓመቱ ለ12 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎች ሞት ምክንያት ናቸው።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እና የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ሃላፊ ኤሪክ ሶልሃይም፥ የአየር ብክለትን፣ የአየር ንብረት ለውጥን እና ፀረ ተሕዋሳት መድኃኒትን የሚቋቋሙ በሽታዎችን በጋራ ለመዋጋት የሚያስችለውን ስምምነት በናይሮቢ ተፈራርመዋል።

ይህ ትብብር የዓየር ንብረት ለውጥ እና የአካባቢ በክለት በጤና ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት ለመቀነስ በሚደረገው ዘመቻ በጋራ ይሳተፋሉ ነው የተባለው።

ይህ ስምምነት ከ15 ዓመታት በላይ በአካባቢ ጥበቃ እና በጤና ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተግባራዊ ሆኖ ይቆያል።

የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ሃላፊ እንዳሉት፥ በአካባቢያዊ ዘላቂነት እና በአየር ንብረት ላይ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቋቋም ሁለቱ ድርጅቶች አንድ ላይ መሥራታቸው በጣም አስፈላጊ ነው ተብሏል።

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው፥ “ጤናችን ከምንኖርበት አካባቢ ጋር ቀጥታ ግንኙነት አለው፤ ይህም በየዓመቱ ከ12 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ሰዎችን የሚገድሉ የተበከለ ውሃና ዓየር እንዲሁም የኬሚካል አደጋዎች እንዳይቀጥሉ በትብብር መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም አብዛኛዎቹ የሚሞቱት በእስያ፣ በአፍሪካ እና በላቲን አሜሪካ በሚገኙ ታዳጊ አገሮች ሲሆን፥ የአካባቢ ብክለት በጤና ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አዲሱ ትብብር ለጋራ ምርምር፣ የልማት መሣሪያዎች እና መመሪያዎችን ማጎልበት፣ የአቅም ግንባታ፣ የዘላቂ ልማት ግቦች ቁጥጥር ማድረግ ዓለም አቀፋዊ እና ክልላዊ የትብብር ማዕቀፍ ይፈጥራል ነው የተባለው።

የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚያመለክተው፥ ሁለቱ ድርጅቶች በስምምነቱ የተጠቀሱትን ተግባርት ለማስፈፀም የሚያስችል የጋራ የሥራ መርሃ ግብር ያዘጋጃሉ።

በተጨማሪም ሂደቱን ለመገምገም በየአመቱ በከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ደረጃ ስብሰባ ያካሂዳሉ፤ በዚህም ቀጣይ ትብብርን በተመለከተ አቅጣጫን ይሰጣሉ።

 

 

ምንጭ፦ WHO