ፆም እና ጠቀሜታዎቹ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለተወሰነ ሰዓት ከምግብና ከመጠጥ መራቅ ወይም መፆም ከሀይማኖታዊ ጥቅሙ በዘለለ በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይነገራል፡፡

ቢያንስ በሳምንት ውስጥ ለሁለት ቀናት መፆም ከጉዳቱ ጥቅሙ እንደሚያመዝንም ነው የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት።

የአብይ ፆም ዛሬ ተጀምሯል፤ ከዚህ አንጻር የጾም ጠቀሜታዎች እንመልከት፦

1. የምግብ መፈጨት ስርዓትን ለማስተካከል

ፆም የምግብ መፈጨት ስርዓትን እረፍት እንዲኖረው በማድረግ የተረጋጋ እና ጤነኛ የስርዓተ ምግብ ዝውውር እንዲኖር ያደርጋል።

የምግብ መፈጨት ስርዓት መስተካከልም በሰውነት ውስጥ የሚገኝን የስብ መጠን ለማቃጠል ይረዳል።

2. ትክክለኛውን የረሃብ ስሜት ለመለየት

መፆም የሰውነት ሆርሞኖች የተስተካከሉ እንዲሆኑ በማድረግ ትክክለኛውን የረሃብ ስሜት እንድንለይ ያደርገናል።

3. የጠራ የሰውነት ቆዳ እንዲኖረን

ፆም ሰውነታችንን ከምግብ መፍጨት ስራው ነጻ ስለሚያደርግ ሆርሞኖቻችን ወደ ሌሎች ስራዎች ይገባሉ።

ለአንድ ቀን ምግብ አለመመገብ ሰውነታችን በውስጡ ያሉትን መርዛማ ንጥረ ነገሮችን እንዲያጸዳ እድል ይሰጠዋል፡፡

በዚህ ጊዜም ኩላሊት፣ ጉበት፣ ቆዳ እንዲሁም ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ተግባራቸውን በአግባቡ እንዲከውኑ ያግዛል።

4. የአዕምሮ የማሰብ አቅምን ይጨምራል

ፆም አዕምሮ ብሬይን ድራይቭድ ኒውሮትራፊክ ፋክተር የሚባል ፕሮቲን እንዲያመርት ይረዳዋል። ይህም አዕምሮ ጤነኛ እንዲሆን ያደርጋል።

በተጨማሪም ፕሮቲኑ ከአዕምሮ ጋር ተያያዥነት ያላቸው እንደ የመርሳት /አልዛይመር እና ፓርኪሰንስ/ በሽታዎችን ይከላከላል።

5. የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ

አልፎ አልፎ መፆም የሰውነትን ክብደት ለመቀነስ እንደሚረዳ ጥናቶች ያመለክታሉ።

ለተወሰነ ሰዓት ከምግብ መራቅ ሰውነት ውስጥ ያለው የስብ መጠን እንዲቃጠል በማድረግ ክብደትን ለመቀነስ ይረዳል።

6. ጥንካሬን ለማግኘት

መፆም የሰውነትን ጥንካሬ እንደሚቀንስ ብዙዎች ያስባሉ።

ይሁን እንጂ ጥናቶች የዚህን ተቃራኒ ያሳያሉ፤ ትንሽ መብላት የመኖር እድሜን ለመጨመር ፋይዳው ትልቅ መሆኑም ነው የሚነገረው።

7. በሽታ የመከላከል አቅምን ይጨምራል

መፆም ሰውነት በሽታ የመከላከል አቅሙን እንዲጨምር ይረዳዋል፤ ይህም በሽታ አምጭ ነገሮች እንዲሁም ካንሰር አምጭ ህዋሶች በሰውነት ውስጥ እንዳያድጉ ያደርጋል።

ጥናቱ ላይ እንደተገለጸው እንስሳት በተፈጥሮ በሚያማቸው ጊዜ ምግብ ከመፈለግ ይልቅ ራሳቸውን ከምግብ በማራቅ እረፍት ይወስዳሉ።

ይህም ሰውነታቸው በቀላሉ በሽታን መከላከል እንዲችል ይረዳዋል።

በተቃራኒው በህመም ወቅት ምግብ ለማግኘት ብዙ የሚለፋው ብቸኛ ፍጡር የሰው ልጅ መሆኑም በጥናቱ ተጠቅሷል።

ፆም ከዚህም ባሻገር መንፈሳዊ ጥንካሬን እንደሚለግስ ተጠቁሟል።

ከዚህ ባለፈም ከእድሜ እና ከልብ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የጤና እክሎችን ለመከላከል እንደሚረዳም ተመራማሪዎቹ ይገልጻሉ።

በድጋሚ የተጫነ

 

 

 

ምንጭ፦ ideadigezt.com