ለስኳር ህመምና ላልተፈለገ ውፍረት ውጤታማ የህክምና አማራጭ ማግኘታቸውን ተመራማሪዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 04፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) ለስኳር ህመምና ላልተፈለገ ውፍረት ውጤታማ የህክምና አማራጭ ማግኘታቸውን ተመራማሪዎች ገለጹ። 

የኮሎራዶ ዩንቨርሲቲ የጤና ትምህርት ክፍል ተመራማሪዎች በአይጦች ላይ በአደረጉት ጥናት በሰውነት ውስጥ ሙቀት የሚያመነጨውን የስብ ክምችት ክፍል ሃይል ምጣኔ በመቆጣጠር ያልተፈለገ የሰውነት ክበደትና የስኳር ህመምን ችግሮችን ለመሻሻል መቻሉን አመላክተዋል።

 ግኝቱ ከዚህ ቀደም ያልተፈለገ የሰውነት ክብደትን ለመቀነስና የስኳር ህመምን ለመቆጣጠር ከሚያስችሉ የህክምና ዘዴዎች ጎን ለጎን በአማራጭነት ሊገለግል እንደሚችል ተመላክቷል።

ያልተፈለገ ውፍረት እና ታይፕ2 የተባለው የስኳር ህመም ተያያዥነት ያላቸው ሲሆን፥ በዚሁ የህክምና አማራጭ መፍትሄ ለመስጠት የሚቻል መሆኑ ተጠቁሟል።

በጥናቱ በሰውነት ውስጥ የስብ ክምችቶችን በሁለት በመክፈል አንደኛው የስብ ዓይነት ሃይል የሚያምቅና 2ኛው ሙቀት የሚያመነጭ መሆኑም ታውቋል።

በአይጦች ላይ ሃይል የሚያመነጨው የስብ ክምችት ክፍል የሃይል አጠቃቀም እንዲመጥን በማድረግ የስኳር ህመምንና ያልተፈለገ የሰውነት ክብደትን ለመቆጣጠር መቻሉን ነው ጥናቱ የሚያመላክተው። 

ግኝቱን ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ሙከራዎች መደረግ ያለባቸው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ተመራማሪዎቹ በሰው ልጅ ህዋሶች ላይ ለመሞከር በዝግጅት ላይ መሆናቸውም ታውቋል።

ምንጭ፦ upi.com

የተተረጎመውና የተጫነው በእንቻለው ታደሰ