በቅዝቃዜ ወቅት ሊደረጉ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እንደ አሁኑ አየሩ ቀዝቀዝ በሚልበት ወቅት የተለየ አለባበስ መከተልና አመጋገብን ማስተካከል እንደሚገባ የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በዚህ ወቅት ሞቅ የሚያደርግ አለባበስን ጨምሮ ሌሎች ጥንቃቄዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልግም ይገልጻሉ።

አለባበስ፦ በተቻለ መጠን ወፍራምና ለብርድ የማያጋልጡ ሹራብና ጃኬቶች መደረብ፥ ለእጅዎም ከንፋስና ቅዝቃዜ የሚከላከሉ ጓንቶችን ማድረግ።

እንዲሁም አንገትዎ ላይ ስካርፍ ነገር ጣል ማድረግና ቤት ከመውጣትዎ በፊት በመጠኑ የፊትና የእጅ ክሬሞችን መቀባት።

እግርን ለነፋስና ብርድ የማያጋልጥ ጫማ መጨማትም በዚህ ወቅት ይመከራል።

በተቻለ መጠንም ከቤት ሲወጡ እርጥበት ከሚያመጡ ነገሮች ራስዎን ማራቅ አለብዎት ምናልባት ለብርድ ብለው የለበሱት ጃኬት ከሞቀዎትና የሚያልብዎት ከሆነም
ለተወሰነ ጊዜ ከፈት አድርጎ ማደራረቅ መልካም ነው።

ይህን ሲያደርጉ ሰውነት የአየሩን ሁኔታ በተሻለ መልኩ እንዲቋቋመው ይረዳዋል። 

በተቻለ መጠንም ሰውነትን ለማሞቅ የሚረዱና ከሱፍና ከጥጥ የተሰሩ አልባሳትን መልበስም በዚህ ወቅት አስፈላጊ ነው።

አመጋገብ፦ አመጋገብም በዚህ ወቅት ሊተኮርበት የሚገባ ሌላኛው ጉዳይ ነው።

በዚህ ወቅት የካሎሪ መጠናቸው ከፍ ያለ እንደ ዳቦ፣ ጥራጥሬ፣ አቮካዶና ሌሎች ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ ሰውነትን ሞቅ እንዳለ እንዲቆይ ይረደዋል።

ከዚህ ባለፈም ከአትክልትና ከስጋ የሚዘጋጅ ሾርባን አዘጋጅቶ መጠጣትና መጠቀም በዚህ ወቅት አስፈላጊና ተመራጭ ነው።

በዚህ መልኩ መመገብ ሰውነት የሚያስፈልገውን ሙቀትና ሃይል ያገኝ ዘንድ ይረዳዋልና ይህንኑ ይከተሉ።

ቤት ውስጥ ሲቀመጡም በተቻለ መጠን ቤቱን ሞቅ ሞቅ ማድረግ ከስራ ወደ ቤት ሲመለሱም ለብ ያለ ውሃ በመጠቀም እጅና እግርን መታጠብ።

ገላዎን መታጠብ በሚፈልጉበት ጊዜ ሰውነትን ሞቅ የሚያደርግ እንቅስቃሴ ካደረጉ በኋላ በቀዝቃዛ ውሃ ቢሆን ይመረጣል።

ምን ጊዜም ቢሆን በቀዝቃዛ ውሃ ሲታጠቡ የተሻለ የደም ዝውውር እንዲኖር በማድረግ በሽታ የመከላከል አቅምዎን ማሳዳግ ያስችልዎታል።

ለብ ባለ ውሃ ቢታጠቡ ለጊዜው ሰውነትዎ ቅዝቃዜ እንዳይሰማው ከማድረግ ባለፈ ዘለቄታዊ መፍትሄ ስለማይሆን በቀዝቃዛ ውሃ መታጠብ ይልመዱ።

ከዚህ ባለፈ ግን ብርዱን ለመከላከል በሚል አልኮል መጎንጨትና በዚህ ወቅት ሲጋራ ማብዛት መልካም አይሆንም።

እነዚህን ነገሮች መከዎን ሰውነት ብርዱን ለመከላከል ከሚያወጣው ሃይል ጋር ተዳምሮ ራስን ለበሽታ የማጋለጥ እድልዎ ከፍ ያለ ይሆናልና ያስወግዱ።

አለባበስዎን በማስተካከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጉም በዚህ ወቅት ሰውነትን ሞቅ ለማድረግ ይረዳል።

በዚህ ወቅት ጉንፋንና ተዛማጅ ህመሞችን ከሚያስከትሉ አጋጣሚዎች ራስን መጠበቅም መልካም ነው።

ምንጭ፦ health.com