ከልክ ያለፈ ውፍረትና የስኳር በሽታ ማከሚያ ዘዴዎች ተገኝተዋል- ተመራማሪዎች

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ተመራማሪዎች አዲስ ባካሄዱት ጥናት የልክ ያለፈ የሰውነት ውፍረት (ክብደት) እና የስኳር በሽታን የማከሚያ ዘዴ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

አዲስ የተገኘው ዘዴም በሰውነታችን ውስጥ ያለውን ሀይል በመቆጣጠር መሆኑንም ተመራማሪዎቹ አስታውቀዋል።

በአሜሪካ ኮሎራዶ ህክምና ትምህርት ቤት በተካሄደው ጥናት የማከሚያ ዘዴው የተገኘ ሲሆን፥ በአይጥ ላይ በተደረገ ሙከራ ስኬታማ መሆኑ መረጋገጡም ተነግሯል።

በሰውነታችን ውስጥ ሀይል የሚያከማቹ እና ሙቀትን የሚያመነጩ ክፍሎች አሉ ያሉት ተመራማሪዎቹ፥ ይህም ሀይል በሰውነታችን ውስጥ እንዲሰራጭ ያደርጋል ብለዋል።

የዚህን ሀይል መጠን በመጨመርም የስኳር በሽታ እና ከልክ ያለፈ የሰውነት ክብደት (የሰውነት ውፍረትን) ለመከላከል ወደሚያስችል ህክምና እንደሚያመራ እምነታቸውን ገልፀዋል።

ክልክ ያለፈ የሰውነት ውፍረት እና ሁለተኛው አይነት (ታይፕ 2) የስኳር በሽታ ግንኙነት አላቸው ያሉት ተመራማሪዎች፥ ከልክ ላለፈ የሰውነት ውፍረት የተጋለጡ ሰዎች በስኳር በሽታ የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑንም ነው የሚናገሩት።

ይህንን ለመከላከልም አመጋገብን ከማስተካከል እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ከመስራት በተጨማሪ፥ የተለያዩ መድሃኒቶችን በመዋጥ እና በቀዶ ህክምና መጠቀም የግድ ነው።

አሁን ያገኙት ዘዴ ግን ይህንን ሁሉ ሊያስቀር የሚችል መሆኑን ያስታወቁት ተመራማሪዎቹ፥ በቅርቡ በሰዎች ላይ ሙከራ በማድረግ ወደ ስራ የሚገባበት መንገድ ላይ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

ምንጭ፦ www.upi.com/Health