በኤምባሲዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ ግለሰቦች በህግ እንዲጠየቁ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ አገራት ባሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጉዳት ባደረሱ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ሃለፊ አቶ ተወልደ ሙልጌታ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው እንዳሉት በተወሰኑ አገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በጥቂት ግለሰቦች ጉዳት ደርሷል።

ለንደን፣ ስቶኮልም፣ አውስትራሊያና ዋሸንግተን ኤምባሲዎች ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የሀገሪቱን ጥቅም የሚያስጠብቁ ከ50 በላይ ሚሲዮናዊያንን በተለያዩ አገራት አሰማርታለች።

ለዲፕሎማት ተቋማትና ግለሰቦች ጥበቃና ከለላ ለመስጠት በተቀረጸው ዓለም አቀፉ የቪየና ስምምነት መሰረት ማንኛውም ሀገር በዚያ አገር ዕውቅና ተሰጥቶት በሚንቀሳቀስ አካል ላይ ህጋዊ ጥበቃ እንዲያደርግ ያስገድዳል።

ይህም በመሆኑ ሁከትና ጉዳቱ የተፈፀመባቸው አገራት በአጥፊዎች ላይ ክስ እየመሰረቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳት ለማድረስ በሞከሩ ግለሰቦች ላይ የአውስትራሊያ መንግስት ክስ የመሰረተ መሆኑንም ነው አቶ ተወልደ የገለጹት።

በለንደን፣ ዋሸንግተንና ስቶኮልም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ላይ ጉዳት ባደረሱ ግለሰቦች ላይም የየአገራቱ መንግስት ህጋዊ ዕርምጃ የመውሰድ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በመንግስት ላይ ቅሬታ ወይም ጥያቄ ካላቸው ኤምባሲዎቹ በሚያዘጋጇቸው የውይይት መድረኮች ማቅረብ ይችላሉ ያሉት አቶ ተወልደ፥

ይህንን ማድረግ የሚያስችል አሰራር መኖሩን እያወቁ በኤምባሲዎች ላይ ህገ-ወጥ ተግባር መፈፀማቸው ትክክል አለመሆኑንም ገልጸዋል።

ሁከቱን በፈጠሩ ግለሰቦች ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በራሱ ከሚወስደው ዕርምጃ በተጨማሪ ኤምባሲዎቹ የሚገኙባቸው አገራት በዓለም አቀፉ ህግ መሰረት አጥፊዎችን ተጠያቂ በማድረግ ላይ ናቸው።

ባለፈው ሳምንት በኒው ዮርክ በተካሄደው 71ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በተጓዳኝ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከሆላንድ፣ ጃፓን፣ ስዊድን፣ ባህሬን፣ ማልታና ሌሎች አገራት ባለስልጣናት ጋር በሁለትዮሽና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

የየአገራቱ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማሩ የሚያስችል ውይይት መደረጉን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ስደተኞችን ከመቀበልና ከማስተናገድ አንጻር ያከናወነችው ተግባር አርአያ መሆኑም በጉባኤው ላይ ተገልጿል።

በ500 ሚሊየን ዶላር ለ100 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እንዲገነቡ የሚያስችል ስምምነት የተደረውም ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ለ30 ሺህ ስደተኞችና ለ70 ሺህ ኢትዮጵያዊያን የስራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑም ታውቋል።

ለግንባታ ከሚያስፈልገው 500 ሚሊየን ዶላር 200 ሚሊየን ዶላሩ በአውሮፓ ህብረት ቀሪው ደግሞ በዓለም ባንክና በሌሎች አገራት ይሸፈናል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በኢትዮጵያ አዲስ ከተሾሙ የህንድ፣ የላይቤሪያ፣ የኡራጓይ፣ የፈረንሳይና አውስትራሊያ አገራት አምባሳደሮች ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውንም አቶ ተወልደ ገልጸዋል።

በተለያየ ምክንያት ከአገራቸው ወጥተው በሌላ አገር እየኖሩ ችግር የገጠማቸው ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በኤምባሲዎችና ቆንስላ ቢሮዎች በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም የጤና ድርጅት አመራርነት በሚያደርጉት ውድድርም የተለያዩ አገሮች ድጋፋቸውን እየገለጹ ይገኛሉ ብለዋል።

ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብና አፍሪካ አገራት ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏልም ነው ያሉት።

 

ምንጭ፦ ኢዜአ