የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 15 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ መሰማራት እንደሚፈልጉ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር አክሊሉ ሀይለሚካኤል፥ የተለያዩ የአሜሪካ ኩባንያዎች ተወካዮችን በዛሬው ዕለት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ ወቅት የኩባንያዎቹ ተወካዮች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ወደ ስራ መግባት እንደሚፈልጉ ለሚኒስትር ዲኤታው ገልጸውላቸዋል።

ሳሄል ግሩፕ፣ አይ ቲ ወርክስ፣ ሲሞናይት ኮምፖዚት፣ ቴራ ፕላንተሪ ሆልዲንግስ፣ ናሽናል ስታንዳርድ ፋይናንስና ሰን ወርክስ ኩባንያዎች፥ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ከሚፈልጉ ኩባንያዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ኩባንያዎቹ በሪል ስቴት፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በአውሮፕላን መገጣጠሚያ፣ በዘመናዊ ግብርና፣ በመሰረተ ልማት ፋይናንስና የሃይል ልማት ቴክኖሎጂ፥ ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል ተብሏል።

ሳሄል ግሩፕ በኢንቨስትመንትና በፋይናንስ አስተዳደር ላይ፣ ሲሞናይት ኮምፖዚት በአልሙኒየም ምርት፣ ቴራ ፕላንተሪ ሆልዲንግስ የአውሮፕላን መገጣጠሚያ እቃዎች ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆን እነዚህ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በስፋት የመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል።

 


ምንጭ፦ ኢዜአ