የሚያሰራ ስትራቴጂ እጦት የከበሩ ማእድናትን ጥቅም አሳንሷል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ኤመራልድ፣ ኦፓል፣ ሳፋየርና ሩቢ የተባሉ የከበሩ ማዕደናት በኢትዮጵያ ይገኛሉ።

እነዚህ ማዕድናት ለጌጣጌጥ መስሪያ እና ለታላላቅ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ለዓለም አቀፉ ገበያ ቀርበው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ማስገኘት የሚችሉ ናቸው።

ለአብነት ኦፓል በአማራ ክልል፣ ሳፋየርና ሩቢ በደቡብና ትግራይ ክልሎች ለበርካታ ሺህ ወጣቶች የስራ እድል ፈጥረዋል።

በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ግን እንደሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የከበሩ ማዕድናት ሀገራዊ፤ ሊያሰራ የሚችል የሀግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ዘርፉ የታሰበውን ያህል ጥቅም ማስገኘት አልቻለም ይላሉ።

አቶ ቴድሮስ ስንታየሁ በማዕድን ዘርፍ ላይ የሚሰሩ ባለሀብት ናቸው፤ እርሳቸው እንደሚሉት የከበሩ ማዕድናት ስትራቴጂ ባለመኖሩ የማዕድን ኢንዱስትሪውን በሚፈለገው ልክ ማሳደግ አልተቻለም።

አቶ ቴድሮስ ኢትዮጵያ ለማዕድን ኢንዳስትሪው የሰጠችው ትኩረት ከሌሎች ኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር ሲነጻጸር የሚቀሩት ስራዎች አሉ ይላሉ።

ዘርፉ ሀገራዊ ስትራቴጂ ወጥቶሎት ባለቤቱ ባለመለየቱ እስካሁን በሀገሪቱ የሚገኙ የከበሩ ማዕድናቱ በጥናት እና በተደራጀ ፍለጋ ሳይሆን በአካባቢው ነዋሪዎች ነው የሚገኙት ብለዋል።

በሀገሪቱ ካሉ የማዕድን ብዛት አኳያ ዘርፉ እንደ ታላቅ ኢንዱስትሪ ተቆጥሮ እሴት የመጨመር ስራ ላይ ስራዎችን እንደ ሀገር መስራት አልተቻለም የሚል እምነትም አላቸው።

እንደ አቶ ቴድሮስ ስንታየሁ ዘርፉ ሊያሰራ በሚችል ስትራቴጂ ቢመራ ጥሬ እቃውን ከመላክ አልፎ እሴት የመጨመር ስራዎችን ለመጀመር ያስችላል።

የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በበኩሉ በከበሩ ማዕድናት ላይ የሚስተዋለው ችግር ምንጩ የስትራቴጂ አለመሆኑን ይናገራል።

በአንጻሩ ሚኒስቴሩ ለዘርፉ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማነስና ምርቱ ለህገወጥ ንግድ የመጋለጡ ችግር መንስኤ የክልሎችና የአካባቢ አስተዳደሮች ቁጥጥር አናሳ መሆን ነው ይላል።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ቴድሮስ ገ/እግዚአብሄር የሚመለከታቸው የክልል፣ የዞንና የወረዳ የመንግስት አካላት ለሰጡት ፈቃድና በሚገኘው ምርት ላይ የሚያደርጉት ቁጥጥር ጠንካራ ከሆነ ዘርፉን ከሚነሱበት ችግሮች ማላቀቅ ይቻላል ይላሉ።

የሚመለከታቸው አካላት ይህን ማድረግ ከቻሉ የፖሊሲ እና የስትራቴጂ ጉዳዮች እንደ ችግር አይነሱም ብለዋል።

በዘርፉ ያለው ቁጥጥር አናሳ ስለመሆኑ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቀደም ባሉት ጊዜያት በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ጉዳት አድርሰው መሰወራቸውን በተመለከተ የሰራቸው ዘገባዎች ማሳያዎች ናቸው።

የማዕድን ዘርፍ ባለሀብቱ አቶ ቴድሮስ ስንታየሁም ዘርፉን ከብክነት ለመታደግ መንግስት ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓትና ሊያሰሩ የሚችሉ የህግ ማዕቀፎችን ሊያወጣ ይገባዋል ብለዋል።

ሆኖም የማዕድን ዘርፉ ለህገ ወጥ ዝወውር መጋለጡንና የታሰበውን ያህል ገቢ እንዳላስገኘ የሚያምነው የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚንስቴር በቀጣይ የቁጥጥር ስራዎች ላይ ከክልሎች ጋር በቅርበት እሰራለሁ ብሏል።


በንብረቴ ተሆነ