በመዲናዋ ተጨማሪ 165 የሸማቾች ማህበራት የስጋ መሽጫ ማዕከላት ሊገነቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲሰ አበባ ከተማ በተመጣጣኝ ዋጋ የስጋ ግብይት እንዲፈፀም የሚያስችሉ የተባሉ ተጨማሪ 165 የሸማቾች ማህበራት የስጋ መሽጫ ማዕከላት ሊገነቡ ነው ተባለ።

የከተማ አሰተዳደሩ የህብረት ስራ ኤጀንሲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮፖሬት እንደገለፀው፥ ተጨማሪ የስጋ መሽጫ ማዕከላት መገንባቱ የሚከበሩ ህዝባዊ በአላትን ተከትሎ የሚያጋጥሙ የዋጋ ጭማሪ እና የአቅርቦት እጥረት ይቅርፋል።

በዚህም ማዕከላቱ በ10 ክፍለ ከተሞች የሚገነቡ ሲሆኑ፥ ከስጋ አቅርቦት በተጨማሪ የኢንዱስትሪ፣ የግብርና እና ሌሎች ምርቶችን የሚያቀርቡ ይሆናል።

እነዚህ ማዕከላት በመዲናዋ ከሚገኙ የግል የመሸጫ ስቆች ጋር በዘመናዊነታቸው የተቀራረበ መሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ስራ ኤጀንሲ የግብይት ዳይሬክተር አቶ ሙሉሸዋ በቀለ ተናግረዋል።

ማዕከላቱ ተገንብተው ወደ ስራ ሲገቡ ከ300 በላይ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር፥ በከተማው የሚታየው የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት እና ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪን በማስቀረት በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይጫወታሉ።

ማዕከላቱ በተያዘው ዓመት መጨረሻ ግንባታቸው ተጠናቆ አግልግሎት እንደሚስጡም ይጠበቃል።

በሀይለሚካኤል አበበ