የቱርኩ ቶስያሊ ኩባንያ በኢትዮጵያ የብረታ ብረት ዘርፍ ለመሰራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ)የቱርኩ ቶስያሊ ኩባንያ በኢትዮጵያ የብረታ ብረት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለ ሚካኤል የኩባንያውን የሥራ ኃላፊዎች በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የቶስያሊ ኩባንያ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ሚስተር ፉአት ቶስያሊ ከሚኒስቴር ዴኤታው ጋር ባደረጉት ቆይታ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ በብረታ ብረት ዘርፍ ለመስራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ነው የገለጹት።

ኩባንያው ለመገንባት ባቀደው ፋብሪካ የኢትዮጵያን የብረታ ብረት ፍላጎት በማሟላት አገሪቷ ምርቱን ከሌሎች አገሮች ለማስገባት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማዳን እንደሚፈልግም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከውጭ አገሮች በብዛት ለግንባታ የምታስገባው ብረት(ቢሌት) ለትንራንስፎርመር አምራች ፋብሪካዎች እንዲሁም የብረታ ብረት ጥሬ ግብዓቶችን ለአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ለማቅረብ በእቅዱ እንደያዘ ጠቁመዋል።

ኩባንያው ከመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር እና የቢዝነስ እና ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመቅረጽ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ስራውን ለመጀመር እቅድ መያዙን አመልክተዋል።

አገሪቷ ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ያለች መሆኗን ጠቁመው፥ በኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት ያላትን አቅም ለመረዳት እንደቻሉም ነው ሚስተር ፉአት ያስረዱት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለ ሚካኤል በበኩላቸው፥ ኩባንያው በአገሪቷ ያለውን የብረታ ብረት ፍላጎት የማሟላት እና ምርቶቹን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ዓላማ ይዞ እንደመጣ ተናግረዋል።

በዘርፉ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች የተወሰነ ጥናት እንዳደረጉ እና ዛሬ ከሰአት በኋላ ከማዕድን ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት አገሪቷ በብረታ ብረት ዘርፍ ስላላት ሀብት እና ዓቅም መረጃ እንደሚያገኙ ገልጸዋል።

ኩባንያው ለአገር ውስጥ መሰል ኩባንያዎች የብረታ ብረት ምርቶች እና ጥሬ ግብዓቶች የሚያቀርብ በመሆኑ "ለሥራ እድል ፈጠራ የሚኖረው ፋይዳ ወሳኝ ነው" ብለዋል።

ኩባንያው ያሳየው ፍላጎት ኢትዮጵያ እና ቱርክ በሁለትዮሽ በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር እንደሆነም ነው ዶክተር አክሊሉ ያስረዱት።

ቶስያሊ ኩባንያ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ሚስተር ፉአት ቶስያሊ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፤ ትናንት ከኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ አህመድ አብተው እንዲሁም ዛሬ ማለዳ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ፍጹም አረጋ ጋር መወያየታቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስት ከሚያደርጉ የውጭ አገር ኩባንያዎች መካከል ከቻይና እና ህንድ በመቀጠል የቱርክ ኩባንያዎች ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል በተለያዩ የስራ ዘርፎች መሰማራታቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያስረዳል።

 

ምንጭ፦ ኢዜአ