አገሪቱ በ2010 ግማሽ በጀት ዓመት ከጎበኟት ቱሪስቶች 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር አግኝታለች

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) በ2010 ግማሽ በጀት አመት ኢትዮጵያን ከጎበኙ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።

ገቢው የተገኘው ሀገሪቱን ከጎበኙ 485 ሺህ 806 የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ነው ብለዋል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም።

ሚኒስትሯ የመስሪያ ቤታቸውን የ6 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ፥ በስድስት ወሩ ከጎብኝዎች የተገኘው ገንዘብ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ10 ነጥብ 8 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል።

ለገቢው ማደግም ሚኒስቴሩ ከውጭ ጉዳይ እና ከሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የሀገሪቱን የቱሪስት መስህቦች ለማስተዋወቅ የሰራው ስራ አስተዋፅኦ ማድረጉን ነው ዶክተር ሂሩት የጠቆሙት።

ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ አለም አቀፍ ቱሪስቶች በኢትዮጵያ የነበራቸው ቆይታ ምን እንደሚመስል የሚጠቁሙ መረጃዎች በመጠይቅ ተሰብስበው መጠናቀቃቸውንም አንስተዋል።

ሚኒስቴሩ እነዚህን መረጃዎች በመተንተንም የጎብኝዎችን የኢትዮጵያ ቆይታ እና እርካታ ለማሳደግ እንደሚሰራ አብራርተዋል።
በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከቱሪዝም ዘርፍ አገሪቱ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዳለች።

 

በፋሲካው ታደሰ