በመዲኗ ከ750 በላይ የማምረቻ ሼዶች ለአዳዲስ የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ሊተላለፉ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ)በአዲስ አበባ ከተማ ከ750 በላይ የማምረቻ ሼዶች ለአዳዲስ የጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራት ሊተላለፉ ነው ተባለ።

በስራ እድል ፈጠራው ላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኘው የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት፥ ሀገሪቱ በማምረቻ ዘርፉ ለማስመዝገብ ያቀደችውን ከፍተኛ ውጤት ለማሳካትም እንዲያግዝ ተደርጎ እየተከናወነ ነው።

በተለይም ወጣቶች እና የስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚዎች በማምረቻ ዘርፉ እንዲሰማሩ ለማበረታታት ከሚደረጉት ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ፥ መሰረተ ልማት የተሟላለት የማምረቻ ቦታ ወይንም ወርክ ሾፕ አንዱ ነው።

በመዲናዋ በጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበር ተደራጅተው በሼዶቹ ውስጥ በመግባት ማምረት መጀመራቸው የነገሩን አስተያየት ሰጪዎች፥ በተሟላለት የማምረቻ ቦታ መግባት መቻል በፍጥነት ወደ ምርት ለመግባት ብቻ ሳይሆን የጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራቱ በግብአት ተመጋጋቢ እነዲሆኑ እና ለትላልቅ ኢንዱሰትሪዎች የሚሆን ግብአት እንዲያቀርቡ ያስችላል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በተገኙበት ዛሬ የተጎበኙት 422 ለማምረቻ ዘርፉ የተዘጋጁ ሼዶችም በተመሳሳይ በክላስተር የተገነቡ ናቸው።

ሼዶቹ በጉለሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ አቃቂ ቃሊቲ እና በቦሌ ክፍለ ከተሞች ይገኛሉ።

ከእነዚህ ሼዶች 357 የሚሆኑትን አዲስ ለተደራጁ እና ስልጠና ለወሰዱ ወጣቶች ለማስተላለፍ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸው ተገልጿል።

እነዚህ ሼዶች ለከተማው ወጣት የስራ እድል ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሚያግዙ ቢሆንም፥ በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት የመሰረተ ልማት አለመሟላት ከባድ ፈተና መሆኑን ከንቲባው ገልጸዋል።

በተለይም ከመብራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች ለሼዶቹ አለመተላለፍ ምክንያት መሆናቸውንም ጭምር ተናግረዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍም የከተማ አስተዳደሩ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ጋር እየተነጋገረ መሆኑንም ነው የተጠቆመው።

በሌላ በኩል የመሰረተ ልማት ተሟልቶላቸው ማምረት የጀመሩ አንዳንድ ማህበራት እንደሚናገሩት፥ ምንም እንኳ ከውጭ ከሚገባው ምርት በተሻለ ጥራት የሚመረት ቢሆንም የገበያ እድል የሚጠበቀውን ያልህ አይደለም።

የከተማ አስተዳደሩ በተለይ በአሁኑ ወቅት እያከናወነ ያለው የክላስተር ሼዶች ግንባታ ይህንን መሰል ችግር ለመፍታት እንደሚያዝግ የተናገሩት አቶ ድሪባ፥ ማህበራቱን ከትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ጋር በማቀናጀት እና አንዳቸው ለአንዳቸው ግብአት አቅራቢ እነዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው።

የከተማ አስተዳደሩ ለማምረቻ ዘርፉ የመሰረተ ልማት ከማቅረብ ባሻገርም ጥራት ያለው ምርት ማምረት እነዲችሉ ተከታታይነት ያለው ስልጠና እና ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ከንቲባው አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ልኡል ሰገድ ይፍሩ በበኩላቸው፥ በአመለካከት የተለወጠ ወጣት እና አመራር ለዘርፉ ስኬታማነት አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ።

የከተማ አስተዳደሩ በዚህ ዓመት በዋናነት በግንባታ እና በማምረቻው ዘርፍ ለ160 ሺህ ሰዎች የስራ እድል ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት 18 ሺህ ወጣቶች በተለያየ ዘርፍ ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸው ሃላፊው ተናግረዋል።

ግንባታቸው ተጠናቀው የመሰረተ ልማት ብቻ የሚጠብቁት 422 ሼዶችም፥ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ መሰረተ ልማቱ ተሟልቶላቸው ከ10 ሺህ በላይ ለሆኑ ስራ ፈላጊዎች ስራ ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የስራ እድል የመፍጠሩ ተግባርም የማምረቻ ሼድ በማያስፈልጋቸው የስራ ዘርፎች ይቀጥላል ነው የተባለው።

 

 

በትእግስት ስለሺ