የህንዱ የሞኔት ኢስፓት ኤንድ ኢነርጂ ኩባንያ በኢትዮጵያ በብረታ ብረት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) የህንዱ 'የሞኔት ኢስፓት ኤንድ ኢነርጂ' ኩባንያ በኢትዮጵያ በብረታ ብረት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል የኩባንያውን የስራ ኃላፊዎች በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የሞኔት ኢስፓት ኤንድ ኢነርጂ ኩባንያ ማኔጅንግ ዳይሬክተርና የህንድ ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ፕሬዝዳንት ሰንዴፕ ጃጆዲያ ከሚኒስትር ዴኤታው ጋር ባደረጉት ቆይታ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ በብረታ ብረት ዘርፍ ለመስራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

ኩባንያው ኢትዮጵያ ከውጭ ለግንባታ የምታስገባውን ከፍ ያለ መጠን ያለው ብረትና የብረታ ብረት ጥሬ ግብዓቶችን ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ለማቅረብ ማቀዱንም ጠቁመዋል።

ኩባንያው ከመንግስት አካላት ጋር በመነጋገርና የቢዝነስና ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመቅረጽ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ስራ ለመጀመር ማቀዱን አመልክተዋል።

ሀሪቷ ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች መሆኗን ጠቁመው፤ በኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ያላትን አቅም ለመረዳት እንደቻሉም ነው ሚስተር ጃጆዲያ ያስረዱት።

ውይይቱን የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቢዝነስና ዳያስፖራ ሚኒስትር ዴኤታ ልዩ አማካሪ አቶ ዮሐንስ ፋንታ እንዳሉት፤ ኩባንያው በብረታ ብረት ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ ያለው በመሆኑ በኢትዮጵያ በዘርፉ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።

ኩባንያው ጥናቱን በማጠናቀቅ "በቅርቡ ወደ ስራ ይገባል" ብለዋል።

የሞኔት ኢስፓት ኤንድ ኢነርጂ ኩባንያ የ25 ዓመታት የስራ ልምድ ያለው ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት በህንድ በዓመት 1 ነጥብ አ5 ሚሊየን ቶን ብረት ያመርታል።

በተጨማሪ በድንጋይ ከሰል ማውጣትና በኃይል ልማት ስራዎች ላይ መሰማራቱም ተገልጿል።

ምንጭ፦ ኢዜአ