የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወርሃዊ የግብይት ዋጋው 4 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ደርሷል

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በታህሳስ ወር 2010 ዓመተ ምህረት 4 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው 105 ሺህ 208 ቶን ምርቶችን ማገበያየቱን ገለፀ።

ምርት ገበያው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ ከጠቅላላ የወሩ ግብይት ውስጥ ሰሊጥ 63 በመቶ በግብይት መጠን እና 50 በመቶ በግብይት ዋጋ ግንባር ቀደም ሆኗል።

የሰሊጥ ግብይት ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር የ17 በመቶ የዋጋ እና የ24 በመቶ የመጠን ጭማሪ አሳይቷል።

የምርቱ የግብይት ዋጋ ባለፈው ወር ከተሸጠበት የ6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

በታህሳስ ወር ከ29 ሺህ ቶን በላይ ቡና በ2 ነጥብ 05 ቢሊየን ብር ግብይት ተፈፅሟል።

ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀርም ቡና የግብይት መጠኑ በ24 በመቶ እና ዋጋው በ29 በመቶ ጭማሪ እንዳስመዘገበ ነው ምርት ገበያው የጠቆመው።

የቡና ዋጋ ካለፈው ወር የ3 ነጥብ 7 በመቶ ካለፈው ዓመት ደግሞ የ4 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።