ከሰጠሁት ብድር የተበላሸውን 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለማስመለስ እየሰራሁ ነው- ልማት ባንክ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከሰጠው ብድር ውስጥ የተበላሸውን 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለማስመለስና መጠኑን ዝቅ ለማድረግ ባበደራቸው ኩባንያዎች ውስጥ የስራ አመራር ድጋፍ እስከማድረግ የደረሰ ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

ባንኩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳለው፥ ካበደረው ገንዘብ ውስጥ መመለሱ የሚያጠራጥረው ወይንም የተበላሸው ብድር በአጠቃላይ ካበደረው ገንዘብ 25 ነጥብ 3 በመቶ ሆኗል።

ባንኩ ካበደረው አጠቃላይ ገንዘብ መመለሱ ጥርጣሬ ውስጥ የወደቀ ወይም ባለሙያዎቹ “የተበላሸ” የሚሉት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከተቀመጠው መስፈርት በላይ ሆኖ ችግር ውስጥ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

በባንኩም ሆነ በተለያዩ ሀገራት አሰራሮች የልማት ባንኮች የተበላሸ ወይም ደንበኞች ተበድረው በተለያየ ምክንያት መመለስ ካለበት የጊዜ ገደብም አልፎ ያልመለሱት ገንዘብ ባንኩ በአጠቃላይ ካበደረው ገንዘብ ከ15 በመቶ መብለጥ የለበትም።

ሆኖም ለልማት ባንክ 15 በመቶ ድረስ ገደብ ተቀመጦለት አሁን ላይ የተበላሸው የብድር ምጣኔ ግን 25 ነጥብ 3 በመቶ የደረሰ ሲሆን፥ ይህም በገንዘብ ሲቀመጥ 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ነው።

ባንኩ ለሰፋፊ እርሻ ኢንቨሰተመንት ከሰጠው 5 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ውስጥ 3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ብሩ የተበላሸ ሲሆን፥ ቀሪው የተበላሸ ብድር ለአምራች ዘፈፉ የሰጠው ነው።

የባንኩ ተቆጣጣሪ ተቋም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፥ ከዚህ ቀደም የተበዳሪዎችን አቅም በታማኝ መረጃ ከማወቅ አንጻር ክፍተት መኖሩ ለዚህ ምክንያት ሆኗል ብለውን ነበር።

የኢትዮያ ልማት ባንክ የስትራቴጂ፣ ለውጥና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ኃይለየሱስ፥ ባንኩ በተለያዩ ዘርፎች ብድር ሰጥቶ አደጋ ውስጥ ያለው ብደሩን ለማስመለስ እና ለመቀነስ ግብረ ሀይል አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ይናገራሉ።

በሰፋፊ እርሻ ዘርፍ ለአዲስ ፕሮጀክቶቸ ብድር በማቆም፣ ነባር ደንበኞቹን በመደገፍና ሀብት የማስመለስ ስራን መሰራት፣ ለአምራች ኢንዱሰትሪ ደንበኞቹም እንዲሁ ቡድን ማቋቋሙን አቶ ክፍሌ ያነሳሉ።

ተበዳሪዎች ምርታማ ሆነው ብድራቸውን መመለስ እንዲችሉ የተለያዩ መንገዶችን ባንኩ እንደሚጠቀም አቶ ክፍሌ ይናገራሉ።

ይህም የብድር መክፈያ ጊዜ ለተጨማሪ ጊዜ ማራዘም፤ የተበዳሪዎች ሁኔታ እተታየ ደግሞ ተጨማሪ የመስሪያ ገንዘብን ማቅረብ እዚው ውስጥ ይገባሉ።

አቶ ክፍሌ ኃይለየሱስ እንደሚሉት ከሆነ፥ የልማት ባንክን የተበላሸ ብድር ምጣኔ ለማስተካከል ባንኩ ሁኔታቸው በአንጻሩ የከፉ ኩባንያዎች የስራ አመራር ውስጥ ጣልቃ በመግባት ክትትልና ድጋፍ እስከማድረግ ይደርሳል።

ከዚህ ሁሉ ድጋፍ ውጭ የሚሆኑት ግን እስከ ሀራጅ ለማድረስ ነው ባንኩ የሚሰራው ብለዋል አቶ ክፍሌ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ካልተመለሰ ብድሩ ጋር በተያያዘ የገባበት ችግር ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የባንኩን የስራ አመራር እስከ መቀየር የደረሰ ሲሆን፥ በአንዳንድ ዘርፎችም ላይ የብድር አሰጣጡ ላይ ለውጥን አምጥቷል።

አሁን ላይም የተበላሸ ብድር ላይ ያለበት ደረጃ ችግር ውስጥ በመሆኑ የማሻሻሉ ነገር ለባንኩ ህልውና ወሳኝ ነው የሚሆነው።

በካሳዬ ወልዴ