ባለፉት 6 ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶች ከ52 ሚልየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ስደሰት ወራት ወደተለያዩ ሀገራት ከላከቻቸው የጨርቃጨረቀ ምርቶች ከ52 ሚልየን በላይ የአሜሪካን ዶላር ገቢ አግኝታለች።

ሀገሪቱ በበጀት አመቱ ከዘርፉ ልታገኝዉ በእቅድ ያስቀመጠችው 93 ነጥብ 6 ሚልየን ዶላር ሲሆን፥ ከዚህ ውሰጥ በግማሽ አመቱ የእቅዱን 52 ነጥብ 2 በመቶ ማሳካት ችላለች።

የጨርቃጨርቅ ልማት ኢንስቲቲዩት ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ባንት ይሁን ገሰሰ ለፋና ብሀሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ የተገኝዉ ገቢ ካለፈዉ አመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነፃፀር በ10 ነጥብ 6 ሚልየን ዶላረ ብልጫ አለዉ።

በአገሪቱ ካሉት 75 የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ፋብሪካዎቸም 58ቱ በወጪ ምርት እየተሳተፉ ሲሆን፥ ከነዚህ ውሰጥም 20ዎቹ የአገር ውስጥ አምራቾች ናቸው።

ወደዉጭ ከሚላኩት ምርቶች መካከለም ክር፣ ያለቀላቸዉ አልባሳት፣ ብትን ጨርቃጨርቆች እና የባህል አልባሳት ሰፊዉን ቁጥር የሚይዙት ናቸው ነው የተባለው።

ጀርመን፣ ጣሊያን፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ አውሮፓ እና አፍሪካ የምርቶቹ ዋነኛ መዳረሻ ሀገራት እነደሆኑ ተመልክቷል።

የጨርቃጨርቅ ልማት ኢንስቲቲዩት የፋብሪካዎቹን አቅም አሁን ካለዉ በተሻለ ለማሳደግ ለፋብሪካዎቹ ባለሙያዎች የክህሎት ስልጠና በዘርፉ ብዙ ልምድ ባካበቱ የህንድ ባለሙያዎቸ እንዲሰጥ እያደረገ ነዉ።

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዘርፉ ተመርቀው ለሚወጡ ተማሪዎች ተጨማሪ ስልጠና በመስጠትም ከፋብሪካዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ላይ እንዳለም ነው አቶ ባንትይሁን የገለፁት።

ከዘመናዊ አሰራር ባህላዊ አሰራርን መከተል፣ ለሀገር ውስጥ ገበያ ዝንባሌ ማሳየት እና አቅምን አሟጦ አለመጠቀም የሚሉ በፋብሪካዎቹ ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶች ሲሆን፥ እነዚህ ችግሮች ባይኖሩ አፈፃፀሙ ከዚህም የተሻለ ይሆን እንደነበር ነዉ የተብራራው።

በዚህ አመት 11 ወደ ምርት ይገባሉ የተባሉ አዳዲስ የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ፋብሪካዎች የነበሩ ቢሆንም፥ ከነዚህ ውስጥ ሰድስቱ ብቻ መጀመራቸዉም ሌላኛዉ በአፈፃፀም ላይ ያጋጠመ ችግር ነው ተብሏል።

ችግሮቹን በመቅረፍ ፋብሪካዎቹን ተወዳዳሪ ለማድረግ እና የዘርፉንም እድገት ለማስቀጠል በየጊዜዉ ክፍተቶች የመለየት ስራዎች እንደሚሰሩ የገለጹት አቶ ባንትይሁን፥ ወደ ስራ ያልገቡ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመርም ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በጋራ እየሰራን ነው ብሏል።

በአጠቃላይ ከጨርቃጨርቅ ዘርፉ በግማሽ አመቱ ለ6 ሽህ ዜጎች አዲስ የስራ እድል እንደተፈጠረም ከተቋሙ ያገኝነዉ መረጃ ያመለክታል።

 

በቤተልሄም ጥጋቡ