የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሁለት ከተሞች በረራ ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኪሳንጋኒ እና ምቡጂ-ማዪ ከተሞች አዲስ በረራ ሊጀምር ነው።

በመጪው መጋቢት የሚጀመረው በረራው አየር መንገዱ በአገሪቷ የሚኖረውን መዳረሻ ወደ አምስት ያሳድገዋል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ወደ ኪሳንጋኒ እና ምቡጂ-ማዪ በረራ መጀመሩ "በዓለም ዓቀፍ በተለይም በአፍሪካ የሚኖረንን የበረራ መዳረሻ የሚያሳድግ ነው" ብለዋል።

ኪንሻሳ፣ ጎማና ሉቡምባሺ ከተሞች በወርቅ፣ ታንታለም፣ ብረታ ብረትና ቆርቆሮ ማዕድናት የበለፀገችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የበረራ መዳረሻዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ላቅ ወዳሉት ኪሳንጋኒና ምቡጂ-ማዪ ከተሞች የሚጀመረው በረራም ደንበኞቹን ከማስደሰቱ ባለፈ አየር መንገዱ በአምስት አህጉር ያለውን ዓለም አቀፍ መዳረሻ ከ100 በላይ ለማድረስ ያስችለዋል ነው ያሉት።

ዋና ስራ አስፈጻሚው በረራውን ወደ ከተሞቹ ለመጀመር የተደረገውን ዝግጅት በቅርበት ሆኖ ሲደግፍ ለቆየው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግስት ምስጋና አቅርበዋል።

አየር መንገዱ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያለውን የበረራ መዳረሻ ለማስፋት እየሰራ ሲሆን፥ በአዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት 2018 የመጀመሪያ ስድስት ወራት 10 ተጨማሪ የበረራ መዳረሻዎችን ለመክፈት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተገልጿል።

በአፍሪካ ግዙፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስካይትራክስ ዓለም ዓቀፍ አየር መንገድ ባለ አራት ኮከብ ምስክር ወረቀት ባለቤት መሆኑ ይታወቃል።

ምንጭ፦ ኢዜአ