በጥር ወር የዋጋ ግሽበቱ ወደ 13 ነጥብ 4 በመቶ ዝቅ ብሏል

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥር ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 13 ነጥብ 4 ሆኖ መመዝገቡን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ መሰረት የዋጋ ግሽበቱ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር የ0 ነጥብ 2 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር የ0 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፥ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ግን የ1 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በጥር ወር የጥራጥሬ፣ የአትክልት፣ የፍራፍሬ፣ የስጋ፣ የወተት፣ አይብና እንቁላል እንዲሁም የዘይትና ቅባት እቃዎች የዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል።

በጥር ወር የተከበሩት የሀይማኖት በዓላት ለምግብ ዋጋ ጭማሪው አስተዋፅኦ ነበራቸው ተብሎ እንደሚታመን ነው ኤጀንሲው በመግለጫው የጠቆመው።