በኦሮሚያ ክልል 6 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 167 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል 6 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 167 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱ ተገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዳስታወቀው፥ ባለሃብቶቹ ከ4 ሺህ 838 ሄክታር በላይ መሬትን እንዲያለሙ ውሳኔ ተላልፏል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ጣሃ ለፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ፍቃድ ከተሰጣቸው 167 ባለሀብቶች ውስጥ 38 በግብርና፣ 102 በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ 21 በማምረቻ እንዲሁም 6 በአገልግሎት ዘርፍ ነው የሚሰማሩት።

በቦርድ ፈቃድ ከፀደቀላቸው ውስጥም 37 ዳያስፖራዎች እና 3 የውጪ ሀገራት ዜጎች የሚገኙበት ሲሆን፥ ቀሪዎቹ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ናቸው።

ባለሃብቶቹ በዚህ በጀት ዓመት ወደ ስራ ሲገቡ፤ ከ10 ሺህ በላይ ቋሚና ከ25 ሺህ በላይ ጊዜያዊ የስራ እድል እንደሚፈጥሩም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ከዚህ ቀደም ባለሃብቶች የተሰጣቸውን ይዞታ አጥሮ በመያዝ ሲፈጥሩ ከነበረው ችግር በመነሳትም ከዞን እስከ ወረዳ የባለሃብቶቹን ወቅታዊ የስራ እቅስቃሴ ለመከታተል የሚያስችል አደረጃጀት መዘርጋቱም ተገልጿል።

 

በታሪክ አዱኛ