በተጨማሪ እሴት ታክስ አዲስ አመታዊ የገቢ ምጣኔ አዲሱ ምዝገባ ተጀምሯል

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 1 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጨማሪ እሴት ታክስ አዲስ አመታዊ የገቢ ምጣኔ መሰረት አዲሱ ምዝገባ ዛሬ ተጀምሯል።

ከዚህ ቀደም አመታዊ ገቢያቸው 500 ሺህ ብርና ከዚያ በላይ የሆነ ነጋዴዎች በተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት ይካተቱ ነበር።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በቅርቡ ያወጣው ህግ ግን አመታዊ ገቢያቸው አንድ ሚሊየን ብርና ከዚያ በላይ የሆናቸው ነጋዴዎች ብቻ በስርዓቱ እንዲካተቱ አድርጓል።

በዚህ አመታዊ የገቢ መለኪያ መሰረት የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋዮች ምዝገባ ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጀምሯል።

ይህ መሆኑ ቀድሞ በነበረው የአመታዊ የገቢ ምጣኔ ይህን ግብር ሲከፍሉ የነበሩ ከአሰራሩ ሲወጡ፥ እንደ አዲስ የሚታቀፉ ነጋዴዎች ደግሞ ወደ አሰራሩ ይገባሉ።

የተሻሻለው አሰራር ከዚህ ቀደም በነበረው ተመን መሰረት ይከፍሉ የነበሩ ነጋዴዎች እየተበራከቱ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ በነበረው የግብር ስርዓት አቅፎ መቀጠል እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ሊከሰት የሚችልን የግብር መጭበርበር እንደሚከላከልም ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በአዲሱ የገቢ ምጣኔ መሰረት በአዲስ አበባ ብቻ ቀድሞ በተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት የሚካተቱ 35 ሺህ ነጋዴዎች ከዚህ ግብር ከፋይነት ሲወጡ፥ ከ31 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ደግሞ ወደ ስርዓቱ የሚገቡ ይሆናል።

በፌደራል ደረጃ ደግሞ የሚታወቁ 30 ሺህ የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋዮች ሲኖሩ፥ በአዲሱ የገቢ ስሌት መሰረት ሁለት ሺህ ግብር ከፋዮች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት እንደሚወጡ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን ምስራቅ አዲስ አባባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

አሰራሩ በአማራ ክልልም ከዛሬ ጀምሮ የተተገበረ ሲሆን፥ ነጋዴዎች አመታዊ ገቢ ምጣኔው ከ500 ሺህ ወደ አንድ ሚሊየን ከፍ ማለቱ እፎይታ የሰጠ ነው ይላሉ።

የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ደግሞ የገቢ ምጣኔው ከፍ ማለቱ ብዙ ዜጎች ንግዳቸውን እንዲያስፋፉ ያግዛቸዋል ይላሉ።

በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ያሉ ነጋዴዎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ ሲሆኑ ስራቸውን እያስፋፉ ወደ ከፍተኛ ነጋዴ እንዲመጡ ስለሚያደርግ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው።

ነጋዴዎቹም ወደ ስርዓቱ መምጣታቸው ስለማይቀር ጉዳዩ ከስራ ፈጠራ ጋር ሊሆን ስለሚችል የረጅም ጊዜ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።

 

 

በታሪክ አዱኛ