አየር መንገዱ ወደ ቻይና በሚሰጠው የጭነት አገልግሎት ተሸላሚ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 2 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና በሚሰጠው የጭነት አገልግሎት ተሸላሚ ሆነ።

አየር መንገዱ ሽልማቱን በቻይናው ጉዋንግዡ ባዩም አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተዘጋጀው የደንበኞች የምክክር መድረክ ላይ ተረክቧል።

ሽልማቱ አየር መንገዱ ወደ ቻይና በሚሰጠው የወጪና ገቢ እቃዎች የጭነት አገልግሎት የተበረከተለት መሆኑን፥ አየር መንገዱ ለጣቢያችን በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ 10 አለም አቀፍና የሃገር ውስጥ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችና ወኪሎች ተገኝተዋል።

በባዩን አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከሚደረገው የጭነት አገልግሎት ውስጥ 13 በመቶ ያክሉ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሸፈን ነው ተብሏል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፥ አየር መንገዱ በዘርፉ ከተሰማሩ አለም አቀፍ ድርጅቶች ተወዳድሮ ተሸላሚ በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው አየር መንገዱ የሚሰጠው የጭነት አገልግሎት እያደገና ስኬት እያስመዘገበ መሆኑንም ተናግረዋል።

አየር መንገዱ በሚሰጠው አገልግሎት ለቻይና-አፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አየር መንገዱ አሁን ላይ በአምስት አህጉራት በሚሰጠው የጭነት አገልግሎት 44 መዳረሻዎች አሉት።

በዚህም በሃገርም ሆነ በአህጉር ደረጃ ለሚደረገው የወጪ ገቢ ንግድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአትክልትና አበባ ምርቶችን ከባህር ዳር ቤልጂየም በሚደረግ የቀጥታ በረራ ማጓጓዝ መጀመሩ ይታወሳል።