የኢትዮጵያ አየር መንገድና የጋናው ጎልድስታር ኤር የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የጋናው ጎልድ ስታር ኤር አየር መንገድ የስታራቴጂክ አጋርነት ስምምነት መፈራረማቸው ተነግሯል።

በስመምነቱም የጋናው ጎልድ ስታር ኤር በኢትዮጵያ አየር መንገድ የጥገና ማእከል እንዲጠቀም የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል።

የጎልድ ስታር ኤር ዋና ስራ አስፈፃሚ አኤሪክ ባነርማን እንደተናገሩት፥ በስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለጎልድ ስታር ኤር የተለያዩ የቴክኒክ እና ኢንጂነሪንግ ድጋፎችን ያደርጋል።

የጎልድ ስታር ኤር ድጋፍ በሚያስፈልገው ጊዜም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለሙያዎች ወደ ስፍራው በማቅናት አስፈላጊውን እገዛ እና ጥገና እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለጋናውያን ባለሙያዎች የተለያዩ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት በጡረታ የተገለሉ የጋና አየር ሀይል ኢንጂነሮች እና የአውሮፕላን አብራሪዎች በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ስልጠና የሚወስዱ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ስራ አስፈፃሚው አክለውም፥ ጎልድ ስታር ኤር አውሮፕላኖች ለአጠቃላይ ጥገና እና ለቀለም ቅብ ስራዎች አዲስ አበባ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጥገና ማእከል እንደሚበሩም አስታውቀዋል።

ጎልድ ስታር ኤር በአሁኑ ጊዜ 12 የተለያዩ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች እንዳሉት ይነገራል።

ከዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹ ውስጥም ከጋና አክራ ወደ ለንደን፣ ዱባይ፣ ጉዋንዙ፣ ባልቶሞር ዋሺንግተን አውሮፕላን ማረፊያ፣ ሌጎስ፣ ኮናክሬ እና ዳካር ይገኙበታል።

ምንጭ፦ www.ghanaweb.com