በስድስት ወራቱ ለገበያ ከቀረበ ከ133 ሺህ ቶን በላይ ቡና በ9 ቢሊየን ብር ተገበያይቷል

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 6 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት ለገበያ ከቀረበ 133 ሺህ 818 ቶን ቡና በ9 ቢሊየን ብር ማገበያየቱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታወቀ።

ምርት ገበያው በዛሬው እለት የስድስት ወራት አፈጻጸሙን ይፋ አድርጓል።

በዚህ ወቅት አጠቃላይ ካገበያየው ውስጥ 42 በመቶው ቡና ሲሆን፥ በዋጋ ደረጃም 62 በመቶውን በማስገባት ቀዳሚውን ድርሻ ይዟል ነው ያለው።

የግብይት መጠኑ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ22 በመቶ ጭማሪ አሳይቷልም ነው ያለው ምርት ገበያው።

በግማሽ አመቱ በምርት ገበያው ከተገበያየው ቡና ውስጥ 82 በመቶ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ መሆኑም ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም ምርት ገበያው በ166 ሺህ 691 ቶን ሰሊጥ፥ 5 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ግብይት መፈጸሙንም ገልጿል።

ግብይቱ ካለፈው ተመሳሳይ አመት አንጻር በመጠን በ42 በመቶ እንዲሁም በዋጋ 114 በመቶ ጭማሪ አሳይቷልም ነው የተባለው።

በምርት ገበያው የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ነጻነት ተስፋዬ፥ በግማሽ አመቱ በምርቶቹ ላይ በግብይቱም ሆነ በምርቱም ላይ መሻሻል መታየቱን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪም በቡና ኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የተደረገው ቁጥጥርና የተወሰደው እርምጃ ግብይቱ ላይ አወንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው የተናገሩት።

ከዚህ በተጨማሪም በምርት ገበያው የቦሎቄና አረንጓዴ ማሾ ገብይቶች ተፈጽመዋል።

ለገበያ የቀረበ 16 ሺህ 734 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ266 ሚሊየን ብር ሲገበያይ፥ ከአጠቃላይ ገቢውም በግብይቱ ሁለት በመቶ በመጠን ደግሞ አምስት በመቶ ድርሻ እንደነበረው ተጠቅሷል።

ባለፉት ስድስት ወራት የዘረጋው የግብይትና አሰራር መዋቅር ለግብይቱ መሻሻል ተጠቃሽ እንደነበርም ምርት ገበያው ገልጿል።

በዚህም የኤሌክትሮኒክስ የጨረታ ግብይት ጥቅም ላይ በማዋል፥ አባል ያልሆኑ ቀጥታ ተገበያዮችን ማስተናገድ መቻሉንም ጠቅሷል።

ምርት ገበያው በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የቆየውን የግብይት ማዕከል በሌሎች አካባቢዎች የማስፋት እቅድ እንዳለውም አስታውቋል።

በዚህም በቀጣዮቹ ወራት በሃዋሳ፣ ሁመራ እና ነቀምት አዳዲስ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማዕከላትን ለመክፈት እየተዘጋጀሁ ነው ብሏል።

አዳማ፣ ጅማ እና ጎንደር ደግሞ የምርት ገበያው ቀጣይ የማስፋፊያ እቅድ አካል ናቸው ተብሏል።

አሁን ላይ 21 ቅርንጫፎችና 60 መጋዘኖች ያሉት ምርት ገበያው በቡሌ ሆራ ቅርንጫፉን ለመክፈትም እየሰራ ነው።

 

 

 

በሃይለሚካኤል አበበ