ሮሂቶ ፋርማሲትካል የተባለው የጃፓን ኩባንያ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎቱ እንዳለው ገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሮሂቶ ፋርማሲትካል የተባለው የጃፓን ኩባንያ በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎቱ እንዳለው አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል የጃፓን ሮሂቶ ፋርማሲትካል ኩባንያ ኃላፊዎችን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ኩባንያው በኢትዮጵያ የዓይን እና የቆዳ እንክብካቤ የመድኃኒቶች ምርት ላይ ለመስራት እንደሚፈልግ ገልጿል።

ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፥ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ የተማረ የሰው ኃይል፣ የገበያ ዕድል እንዲሁም የኃይል አቅርቦት መኖሩ ባለሃብቶቹን ውጤታማ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።

የመድኃኒት ማምረቻ አንዱ የኢትዮጵያ የትኩረት መስክ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር አክሊሉ፥ ለዚሁ የተዘጋጀ የኢንዲትሪ ፓርክ በቅሊንጦ እየተገነባ ነው ብለዋል።

በዚህም ሮሂቶ ፋርማሲትካል በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረጉ መድሃኒትን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስፈልገውን ወጭ እንደሚቀንስ እና በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

የሮሂቶ ፋርማሲትካል ኩባንያ ልዕኳን ቡድን መሪ እና የኩባንያው ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሱና ያን በበኩላቸው፥ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ የዓይን እና የቆዳ እንክብካቤ የመድኃኒቶች ማምራት ላይ ለመስራት እንደሚፈልግ ጠቅስው ኢትዮጵያ ያላት የኢንቨስትመንት ዕድል እና ድጋፍ መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

ኩባንያው በዘርፉ ካሉት የኢትዮጵያ ባለሃብቶብች ጋር ለመስራት እና ምርቱን ለምስራቅ አፍሪካ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ እንዳለው መግለፁም የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያደረሰን መረጃ ያሳያል።

በተያያዘ ዜና የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የሚያደርጉት የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲያስፋፉ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ፌቱህ ኤሉሰይ አስታወቁ።

29178872_2132964986936496_1232372884844838912_n.jpg

አምባሳደር ኤሉሶይ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ዲፕሎማቶችና የፓርላማ አባላት እየተሰጠ ባለ ስልጠና ላይ እንደገለጹት፥ ቱርክ የሀገራቸው ባለሃብቶች በኢትዮጵዩ ያላቸውን የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ታበረታታለች ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ ያስመዘገቡ የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በዚህም ለ30 ሺህ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል ፈጥረዋል።

ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት በመጠቀም የንግድና ኢኮኖሚ ትስስራቸውን የበለጠ ለማሳደግ መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።