በአዲስ አበባ ሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 74 የንግድ ድርጅቶች ታሸጉ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 27፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉና ህገ-ወጥ ተግባራትን በፈፀሙ 74 ህገ-ወጥ ነጋዴዎች የንግድ ድርጅታቸው መታሸጉን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የድህረ ፈቃድ ኤንስፔክሽን ሬጉላቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን በየነ ፥ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ፣ ምርቶችን በመጋዘን የደበቁ፣ ያለ ንግድ ፈቃድ ሲሰሩ በተገኙ፣ በድጎማ በቀረቡ የሸማች ዘይት እና ስኳር ላይ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 74 የንግድ ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም ለ122 የንግድ ድርጅቶች የቃል ማስጠንቀቂያና ለ148 የንግድ ድርጅቶች ደግሞ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

የመሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች አቅርቦትን በተመለከተ ወርሃዊ ኮታ 165 ሺህ 657 ኩንታል ስንዴ፣ 120 ሺህ ኩንታል ስኳር እንዲሁም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር በላይ ዘይት መቅረቡን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

በተለይ የስንዴ ስርጭትን በተመለከተ 165 ሺህ 657 ኩንታል ስንዴ 40 ለሚሆኑ ድርጅቶች እንደተሰራጨ የተነገረ ሲሆን፥ 22 በሚሆኑ መጋዘኖች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ቢሮው እርምጃ መውሰዱ ተገልጿል፡