ኢትዮ ቴሌኮም በ47 የአጭር ቁጥር ጽሁፍ መልዕክት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ እርምጃ ወሰደ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 27፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም የህብረተሰቡን ቅሬታ መሰረት አድርጎ በ47 የአጭር ቁጥር ጽሁፍ መልእክት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

የኢትዮ ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አብዱራሂም አህመድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ እርምጃው የተወሰደው ከህብረተሰቡ በሚነሳው ቅሬታ ላይ ተመስርቶ ነው።

አቶ አብዱራሂም፥ ከአጭር ቁጥር (Short code) የጽሁፍ መልእክት ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ከደንበኞች የሚቀርቡ ቅሬታዎች አሉ ብለዋል።

ከቅሬታዎቹ መካከል በተለይም ያለደንበኞች ፍላጎት መልእክት መላክ እና ከተላከ በኋላም ገንዘብ መቁረጥ ሳይፈቀድ ገንዘብ መቁረጥ እንደሚገኝበት እንስተዋል።

እንዲሁም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የገቡትን ስምምነቶች በተደጋጋሚ በመጣስ ማድረግ ያለባቸውን ነገሮች ሳያደርጉ የቀሩ እና የተከለከሉትን ነገሮች ደግሞ የመጣስ ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል።

በእነዚህ እና ሌሎች ከህብረተሰቡ በሚነሱ ቅሬታዎች ላይ በመመስረትም ወደ 47 የሚደርሱ የአጭር ቁጥር የጽሁፍ መልዕክት አገልግሎት ሰጪዎች እንዲቋረጡ መደረጉን አስታውቀዋል።

በቀጣይም የገንዘብን ጨምሮ ሌሎች ቅጣቶች በእነዚህ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ ተፈፃሚ እንደሚደረጉም አስታውቀዋል።