በምግብ መጠጥ እና እና ፋርማሲዩቲካል ዘርፎች በዚህ ዓመት 45 ሺህ ቋሚ የስራ ዕድል ተፈጥሮዋል - ፋርማሲቲካል ኢንደስትሪዎች ልማት ኢኒስቲትዩት

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምግብ መጠጥ እና እና ፋርማሲዩቲካል ዘርፎች በዚህ ዓመት ብቻ ከ45 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል መፈጠሩን የምግብ መጠጥ እና ፋርማሲቲካል ኢንደስትሪዎች ልማት ኢኒስቲትዩት አስታወቀ፡፡

 

ተቋሙ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከዉ መረጃ ለዜጎቹ የተፈጠረዉ የስራ እድል በአገዳ እህሎች ፕሮሰሲንግ፣ በቅባት እህሎች፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም በመጠጥ ምርት እና ፓኬጂንግ በመሳሰሉ ዘርፎች መሆኑን ገልጿል፡፡

ከዚህ ውስጥ ከ20 ሺህ በላይ የሚሆነው በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንደስትሪዎች የተፈጠረ የስራ እድል ነው ተብሏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ በተለይ በመካከለኛ ኢንዱስትሪዎችም የግብዓት አቅርቦት ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ በዘርፎቹ ከ18 በላይ አዳዲስ የስራ እድሎች መፍጠር መቻሉንም ገልጿል።

በአነስተኛ ኢንደስትሪዎች በማሳተፍም እጽዋትን በማቀናበር ስራ የመሰሉ ከ8 በላይ አዳዲስ የስራ ዘርፎችን ለማካተት መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ተቋሙ አቅዶት ከነበረዉ የስራ እድል ፈጠራ ከ80 በመቶ በላይ ማሳካት መቻሉን ገልጿል፡፡

ሆኖም በየዘርፎቹ በሚያጋጥመው የግበዓት አቅርቦት እጥረት፣ የቦታ ችግር እና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት ዘርፎቹ በሚፈለገው ልክ ውጤታማ እንዳይሆኑ እና የስራ እድሎች እንዳይስፋፉ እክል መሆኑንም ነው ተቋሙ ያስታወቀው።