አየር መንገዱ በፈረንጆቹ 2017/18 አመት 233 ሚሊየን ዶላር የተጣራ ትርፍ አገኘ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 4 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፈረንጆቹ 2017/18 አመት 233 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።


የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም፥ አየር መንገዱ በፈረንጆቹ 2017/18 አመት የተጣራ 233 ሚሊየን ዶላር ትርፍ ማግኘቱን ተናግረዋል።

ካለፈው አመት አንጻር የ4 ሚሊየን ዶላር ብልጫ ማሳየቱንም ነው የተናገሩት።

ትርፉ አየር መንገዱ በሰጠው ከ10 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ የመጓጓዣ እና ከ400 ሺህ ቶን በላይ የጭነት አገልግሎት የተገኘ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም የአየር መንገዱ አጠቃላይ ገቢ 43 በመቶ እድገት ማሳየቱን ጠቅሰዋል።

የጭነት አገልግሎቱ 18 በመቶ የመንገደኞች ቁጥር ደግሞ 21 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንም አስታውቀዋል።

ተጨማሪ 14 አውሮፕላኖችን በማስገባት 10 አዳዲስ መዳረሻዎች መክፈቱንም አንስተዋል።

አሁን ላይም አየር መንገዱ ባሉት ከ100 በላይ አውሮፕላኖች በ115 መዳረሻዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በዙፋን ካሳሁን