አየር መንገዱ የቻድ አቻውን 49 በመቶ ድርሻ ሊገዛ ነው

አዲስ አበባ ነሀሴ ፣5፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቻድ አየር መንገድን የ49 በመቶ ድርሻ ሊገዝ መሆኑ ተገለፀ።

አዲሱ የቻድ አየር መንገድ በፈረንጆቹ 2019 ጥቅምት ወር ሥራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

አዲስ የተቋቋመውን የቻድ አየር መንገድ 51 በመቶ የሚሆነውን የባለቤትነት ድርሻ የቻድ መንግስት የሚቆጣጠር ሲሆን፥ ቀሪውን 49 በመቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በሽርክና ለመያዝ ውይይት እየተካሄደ መሆኑ ተነግሯል።

በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመካከለኛው አፍሪካ ለሚሰጠው የበረራ አገልግሎት የቻድ አየር መንገድን ማዕከል አድርጎ ይሰራል ተብሏል።

አየር መንገዱ በተጨማሪም የጅቡቲን፣ የኢኳቶሪያል ጊኒን እና የጊኒን አየር መንገዶች በሽርክና ለመያዝ እየተነጋገረ ነው ተብሏል።

ከዚህ በፊት አየር መንገዱ የቶጎ አየር መንገድን 40 በመቶ፣ የማላዊ አየር መንገድን ደግሞ 49 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ በመያዝ እየሰራ እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው።

እንዲሁም በቅርቡ ስራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀውን የዛምቢያን አየር መንገድ 45 በመቶ ድርሻ ባለፈው ጥቅምት ወር መግዛቱ ኢስ አፍሪካ በዘጋበው አስታውሷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፈረንጆቹ 2017/18 አመት 233 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን በትናትናው ዕለት ይፋ አድረጓል።

ትርፉ ካለፈው አመት አንጻር የ4 ሚሊየን ዶላር ብልጫ ማሳየቱንም ነው የተነገረው።

ይህ ትርፉ አየር መንገዱ በሰጠው ከ10 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ የመጓጓዣ እና ከ400 ሺህ ቶን በላይ የጭነት አገልግሎት የተገኘ መሆኑንም ተነግሯል።