ከዓይኖቿ የጥጥ እንባ የምታወጣው ህንዳዊት ታዳጊ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህንዳዊቷ ታዳጊ ካለፉት ሁለት ሳምንት ጀምሮ የጥጥ እንባ ከዓይኖቿ እየወጣ መሆኑ ብዙዎችነ እያነጋገረ ነው።

የማድያ ፕራዴሽ ግዛት ነዋሪዋ ስሟ ማናሲ ትባላለች፤ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በየቀኑ ከዓይኖቿ ከ35 እስከ 40 የሚደርሱ ጥጥ መሳይ ነጭ ነጥብጣቦች በእንባ መልክ እየወጣ ነው።

የ11 ዓመቷ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ማናሲ፥ የጥጥ እንባዋ መውጣት የጀመረው ካሳለፍነው የፈረንጆች ነሃሴ 25 ጀምሮ ነው።

አባቷና የአካባቢው ሰዎች በሁኔታው ተደናግጠው የሙት መንፈስ በሰውነቷ ተሰራጭቶ ነው እሰከማለት ደርሰዋል።

የመንደሩ ነዋሪዎች ስለ ማናሲ አዲስ አጋጣሚ ወሬውን ከሰሙ ጊዜ ጀምሮ ታዳጊዋን እና ቤተሰቦችን አግልለቸዋል።

ሌሎች ሰዎች ደግሞ አባት ጌንድንላል ኬቫት ልጃቸውን ወደ ዓይን ሃኪሞች ቢወስዷት የተሻለ መሆኑን ከመምከር አልተቆጠቡም።

በአካባቢው የሚገኙ አንድ ሃኪም ሁኔታውን ከሰሙ በኋላ ወደ ታዳጊዋ ቤት ይሄዳሉ።

በስፍራው ደርሰውም ከዓይኖቿ የሚወጡ የጥጥ ነጠብጣቦችን ከመረመሩ በኋላ የዓይን ስፔሻሊስቶች ቢያዩዋት የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል።

ማናሲ የተለያዩ የዓይን ህክምና ቦታዎችን ያዳረሰች ሲሆን፥ አዲሱ የእንባዋ ጉዳይ ደግሞ በርካታ የዓይን ሃኪሞችን አነጋግሯል።

በጃባልፑር የህክምና ኮሌጅ የዓይን ህክምና ትምህርት ክፍል ሃላፊው ዶክተር ናቭኔት ሳክሴና፥ የእንባዎቹ ወደ ጥጥ ነጠብጣብ መለወጥ ምናልባት ከሰውነቷ የባዕድ ነገር ጠልነት ጋር የተገናኘ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

ዶክተር ፓዋን ሴታክ የተባሉ የዓይን ሃኪም በበኩላቸው፥ ክስተቱ ከቫይታሚን ዲ እጥረት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ነው የገለፁት።

የተመጣጠነ ምግብ የማይመገቡ ልጆች በዓይኖቻቸው ዳርቻ ነጭ ነጠብጣቦች ይታያሉ፤ ይህም የማናሲ ጉዳይ ከዚህ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል ነው ያሉት ዶክተር ፓዋን።

ሃኪሞች ከልምዳቸውና ካላቻው እውቀት አኳያ ግምታቸውን ቢያስቀምጡም የማናሲ ዓይኖች ግን አሁንም ጥጥ እንባ ከዓይኖቿ ሲያፈልቁ ይውላሉ።

ከዚህ በፊት አንድ የመናዊት ታዳጊ ከዓይኖቿ የድንጋይ እንባ እንደምታወጣ መነገሩ ይታወሳል።

ላውራ ፖንስ የተባሉ ሰው ደግሞ ለ20 ዓመታት ያህል ብርጭቆ መሰል ጠጣር ቁሶች በእንባ መልክ ሲወጡ እንደነበር የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ መሳቡ አይዘነጋም።

ምንጭ ኦዲቲ ሴንትራል