የልጃቸውን ህይወት የታደጉላቸውን ሃኪሞች 1 ሺህ 500 ዩዋን ካሳ የጠየቁት ቻይናዊ…

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የልጃቸውን ህይወት የታደጉ ሃኪሞችን “የልጄን ልብስ በመቅደዳችሁ 1 ሺህ 500 ዩዋን ካሳ ልትከፍሉኝ ይግባል” ያሉት ቻይናዊ ጉዳይ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።

ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው፤ በሀገረ ቻይና አንድ ልጅ ድንገት ልቡ መምታት ያቆምና ራሱን ስቶ ይወድቃል።

በዚህ ጊዜም ድንገተኛ ህክምና እንዲደረግለት ወደ ሆስፒታል ይወሰዳል።

ድንገት የታመመው ሰው እድለኛ ሆኖ በሁቤይ ግዛት የሚገኘው የዦንግናን ሆስፒታል ሃኪሞች ባደረጉት ጥረት ህይወቱ ትተርፋለች።

ሆኖም የታማሚው አባት ለሃኪሞቹ ምስጋናን ሳይሆን የበደል ካሳን ጠይቀዋል።

ሃኪሞች ለታመመው ልጅ ድንገተኛ ህክምና ሲሰጡ ልብሱን በመቅደዳቸው የተነሳ ነው ካሳውን የጠየቁት።

ይህ አይነቱ ክስተት በመሰል ህክምናዎች የተለመደ ቢሆንም፥ አባት ግን “የልጄን ልብስ ስለቀደዳችሁ ለልብሱ ካሳ 1 ሺህ 500 ዩዋን ልትሰጡኝ ይገባል” የሚል ጥያቄን አቅርበዋል።

በቻይናው የዌይቦ ማህበራዊ ትስስር ገፅ በወጡ መረጃዎች መሰረት፥ የታማሚው የማንነት መታወቂያ ካርድ እና ሌሎችም ንብረቶች ከኪሱ ጠፍተዋል ተብሏል።

በርካታ የማህበራዊ ትስስር ገፁ ተጠቃሚዎች የልጁ አባት ሃኪሞች የልጁን ህይወት ስለታደጉለት ምስጋና ማቅረብ ሲገባቸው፥ ልብሱን ስለቀደዳችሁ ካሳ ልትሰጡኝ ይግባል ማለታቸውን ተቃውመዋል።

አባት ከልጃቸው ደህንነት ይልቅ ለልብሱ ማዘናቸውም በርካቶችን አሳዝኗል ነው የተባለው።

ሻንጋይስት የተባለ ድረገፅ እንዳስነበበው አንድ ሃኪም ለታማሚው አባት 1 ሺህ ዩዋን የሰጣቸው ሲሆን፥ ጭንቀታቸውን እንደተረዳ መግለጹ ተነግሯል።

“ለተወሰኑ ሰዎች 1 ሺህ ዩዋን ጥቅሙ ብዙ ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም ለታማሚው አባት ገንዘቡ ምናልባት ሊጠቅማቸው ይችላል” ማለቱ በሻንጋይስት ድረ ገፅ ላይ ሰፍሯል።

 

 

 

 

ምንጭ፦ www.ndtv.com