በፖሊስ የሚፈለገው ወጣት ራሱን አሳልፎ ለመስጠት ለፖሊሶች ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ አነጋጋሪ ሆኗል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በፖሊስ የሚፈለገው ወጣት ፖሊስ በፌስቡክ የሚለቀው መረጃ 1 ሺህ ጊዜ ከተጋራ ራሱን አሳልፎ እንደሚሰጥ ቃል በገባው መሰረት በፖሊስ ዋና መስሪያቤት መገኘቱ ብዙዎችን አነጋጋሪ ሆኗል።

የሚቺጋን ነዋሪው በፈፀመው ጥፋት በፖሊስ እንደሚፈለግ ማወቁን ተከትሎ ለፖሊስ ያልተለመደ አይነት ትዕዛዝ አስቀምጧል።

ይህ ያልተለመደ ትዕዛዝም ፖሊስ በፌስቡክ የሚለጥፈው መረጃ በ1 ሺህ ሰዎች ከተጋራ ራሱን አሳልፎ እንደሚሰጥ እና ለፖሊሶችም ዶናት እንደሚያመጣላቸው ቃል መግባቱን የሚገልፅ ነው።

ሚካኤል ዘይድል የ21 ዓመት ወጣት ነው።

ከዚህ ቀደም በፈፀመው ጥፋት በፖሊስ መፈለግ ይጀምራል።

ፖሊስ ዛይድል ባጠፋው ጥፋት ምክንያት እንደሚፈለግ እና ሰዎች ወጣቱ ያለበትን እንዲጠቁሙት በፌስቡክ ያሳውቃል።

በፌስቡክ በተለጠፈው የፖሊስ መረጃ ላይ ምላሽ ከሰጡ ሰዎች ውስጥ አንዱ ዛይድል ነበር።

ዛይድል በምላሹ “ፖሊስ ሆይ በፌስቡክ ያወጣሃው መረጃ 1 ሺህ ጊዜ ከተጋራ እኔ ራሴ መስሪያ ቤታችሁ ድረስ እመጣለሁ የሚል ነበር።

ወጣቱ ከዚህብ በላይ ፖሊስ የተቀመጠለትን መስፈርት ካሟላ ዛይድል ለፖሊስ አባላቱ ዶናት ይዞላቸው እንደሚሄድ ነበር የፃፈው።

ፖሊስም ይህን ምላሽ እንዳየ በመጠራመጠር እና በበለጠ ተስፋ ውስጥ ሆኖ “እባካችሁ የፌስብክ ቤተሰቦች እኛ 1 ሺህ ማጋራት እንድናገኝ እርዱን” የሚል ንቅናቄ ጀመሩ።

በዚህም የዛይድልን “ይፈለጋል ዘመቻ” ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች በፌስቡክ የማህበራዊ ትስስር ገፅ አጋሩት።

ይህን ያረጋገጠው ዛይድልም ራሱን ለፖሊስ አሳልፎ ሰጠ።

በዋና መስሪያ ቤቱ ያለማንም አስገዳጅ አንድ ሻንጣ ሙሉ ዶናት እና ዶንቦሊኖ ለፖሊሶች ይዞላቸው ሂዷል።

ሚካኤል ዛይድል ቃሉን ቢጠብቅም፥ ፍርድ ቤት በእስር እንዲቆይ ከፈረደበት የ39 ቀናት ቅጣት በተጨማሪ የተወሰነበትን ክፍያ ካልፈፀመ በ30 ቀናት ሊያራዝምበት የሚችል ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

 

 

ምንጭ፦ኦዲቲ ሴንትራል