ተማሪ እያለ ከእናቱ ጋር የገባውን ስምምነት ያፈረሰው ልጅ 1 ሚሊዮን ዶላር ለእናቱ እንዲከፍል ተፈረደበት

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታይዋን ተማሪ እያለ ከእናቱ ለትምህርት የተከፈለለትን ገንዘብ እንዲመልስ የገባውን ውል ያፈረሰው ልጅ 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍል የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ፈርዶበታል።

ከባለቤታቸው ጋር በመፋታታቸው ሁለት ልጆቻቸውን ብቻቸውን ያሳደጉት እናት፥ ልጆቻቸው ተምረው ራሳቸውን ሲችሉ የሚንከባከበኝ ሰው አጣ ይሆናል በሚል ስጋት ከልጆቻቸው ጋር ውል ለመግባት ይወስናሉ።

እናት ሁለቱ ልጆቻቸው ትምህርታቸውን አጠናቀው ስራ ሲጀምሩ ለትምህርት ያወጡሏቸውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ እስኪከፍሏቸው ድረስ ከገቢያቸው 60 በመቶውን እንዲሰጡ ውል አስፈርመዋቸው ነበር።

ልጆቹ እናት ከቤተሰባቸው ባገኙት ገንዘብ በከፈቱት የጥርስ ክሊኒክ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሲሆን፥ ልጆቹ ለረዥም ጊዜ የገቢያችንን አብዛኛውን በዚህ መልኩ መክፈል የለብንም የሚል አቋም ይይዛሉ።

አንደኛው ልጃቸው በድርድር መጠኑን አስቀንሶ ክፍያውን ቢቀጥልም አንደኛው ግን ሙሉ በሙሉ ክፍያውን ለማቆም በመወሰኑ እናት ጉዳዩን ፍርድ ቤት ወስደዋል።

ለስምንት ዓመታት የእናትና ልጅ ክርክር ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ደርሷል።

ቀደም ሲል በውሉ መሰረት 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለእናቱ መክፈሉን የገለፀው ልጅ ይህ በቂ መሆኑን እና ውሉን ሲገባ 20 ዓመት ወጣት እንደነበር እና የውሉን ስሜት በቅጡ ሳይረዳ መፈረሙን በማንሳት ተከራክሯል።

ሆኖም ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ልጅ ከእናቱ ጋር የገባው ውል ተፈፃሚነቱ አስገዳጅ በመሆኑ፥ ለትምህርት 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር ላወጡለት እናቱ ቀድሞ ከከፈለው ውጪ 1 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ እንዲከፍል ፈርዶበታል።

 

ምንጭ፦www.odditycentral.com