አሜሪካዊው ግለሰብ ጠጥቼ እያሽከረከርኩ ነው ሲል ለፖሊስ ደውሏል

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ከተማ ነዋሪ የሆነው የ39 ዓመቱ ሚካኤል ሌስተር በሰራው ስራ የፖሊሶችን ስራ አቅልሏል ተብሏል።

የ39 ዓመቱ ሚካኤል ሌስተር በአውሮፓውያኑ 2018 አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ አልኮል ከመጠን በላይ ጠጥቶ መኪና እያሽከረከረ መሆኑን በራሱ ደውሎ ለፖሊስ በማመልከቱ ነው የፖሊስን ስራ አቅልሏል የተባለው።

ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው፤ ሚካኤል ወደ 911 የጥሪ ማእከል ይደውላል፤ የስልኩ ኦፕሬተርም ፈልጎ እንደደወለ ስትጠይቀው፤ “በጣም ጠጥቼ እያሽከረከርኩ ነው” ሲል ይመልስላታል።

ኦፕሬተሯ ግለሰበቡ ያለበትን ቦታ ስትጠይቀውም፤ “ከመጠን በላይ ስለጠጣው ያለውበትን አላውቅም” ሲል መልሶላታል ነው የተባለው።

በወቅቱም ግለሰቡ በተሳሳተ አቅጣጫ በኩል እያሽከረከረ መሆኑ ለፖሊስ መረጃ ይደርሰዋል።

መረጃው የደረሳቸው ፖሊሶችም በፍጥነት ሚካኤል ወዳለበት አካባቢ በማምራት ምንም አይነት አደጋ ያሳደርስ ሊያስቆሙት ችለዋል ነው የተባለው።

በወቅቱ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ሚኪኤል ጠጥቶ በማሽከርከር፣ በተሳሰሳተ አቅጣጫ በማሽከርከር፣ አካፋይ የጎዳና መስመሮችን አላግባብ በመጠቀም እና ያለ ደህንነት ቀበቶ በማሽከርከር የሚሉ ክሶች ቀርበውበታል ነው የተባለው።

ምንጭ፦ www.ndtv.com