በስህተት በተሸጠላት የሎተሪ ትኬት 5 ሚሊየን ዶላር ያሸነፈችው አሜሪካዊት

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አሜሪካዊቷ ግለሰብ ያለፍላጎቷ በስህተት በተሸጠላት የሎተሪ ትኬት አማካኝነት ሚሊየነር ሆናለች።

እድለኛዋ ኦክሳና ዘሃሮፍ ትባባላች፤ በኒው ዮርክ የሚገኝ ሱፐር ማርኬት ውስጥ እቃ በመግዛት ላይ እያለች በመሃል ባለ 1 ዶላር የሚፋቅ ሎተሪ ለመግዛት ታቀናለች፤ ሆኖም ግን የሽያጭ ባለሙያ በፈጠረው ስህተት ባለ 10 ዶላር የሎተሪ ትኬት ይሰጣታል።

ምንም እንኳ ያልፈለገችው የሎተሪ ትኬት ቢሰጣትም፤ 10 ዶላሩን ከፍላ ሎተሪውን ለመውሰድ ትወስናለች።

ኦክሳና ዘሃሮፍ ለኒው ዮርክ ሎተሪ አስተዳደር ትናገራለች፥ “የሽያጭ ባለሙያው የተሳሳተ የሎተሪ ትኬት ሲሰጠኝ ተናድጄበት ነበር፤ ነገር ግን 10 ዶላር ከፍዬ ትኬቱን ወሰድኩት” ብላለች።

ሆኖም ግን የሎተሪ ትኬቱን ወዲያውኑ ከመፋቅ ይልቅ ሌላ አላማ ስትጠቀመውም ቆይታለች።

ኦክሳና ዘሃሮፍ፥ “ሎተሪውን ለመፋቅ ከመወሰኔ በፊት ለሁለት ሳምንታት ያክል እንደ ማስታወሻ መያዢያነት ስጠቀምበት ነበር” ብላለች።

በመጨረሻም ቀኑ ደርሶ ሎተሪውን ስትፍቅ ያልጠበቀችው ነገር ያጋጥማታል፤ ይህም የ5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር አሸናፊ መሆኗን የሚያበስር መሆኑ ነበር።

“ከዚህ በፊት ምንም ነገር አሸንፌ አላውቅም፤ ትኬቱን ወደ ሎተሪ አስተዳደር ቢሮ አምጥቼ እስካሳየው ድረስም እውነት አለመሰለኝም ነበር” ብላለች ኦክሳና ዘሃሮፍ።

በሎተሪው ምክንያት የተፈጠረው አጋጣሚም በርካቶችን ያስገረመ ሲሆን፥ የዓለማችን የምንጊዜውም ምርጡ ስህተት ተብሎለታል።

ምንጭ፦ www.ndtv.com