2ኛ ወለል ላይ ከሚገኝ ግድግዳ ጋር የተጋጨው ተሽከርካሪ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ተሽከርካሪ ከግንብ ጋር ተጋጨ የሚል ዜና ምንም እንኳ የተለመደ ቢሆንም፤ ከወደ ካሊፎርኒያ የተሰማው ወሬ ግን በርካቶችን አስገርሟል።

በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ በደረሰው የትራፊክ አደጋ አንድ ተሽከርካሪ ሁለተኛ ወለል ላይ ከሚገኝ ግድግዳ ጋር መጋጨቱ ነው አግራሞትን የፈጠረው።

የአካባቢው የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ ባለስልጣን ሰራተኞች ያነሱት ፎቶግራፍም፥ ነጭ የቤት ተሽከርካሪ በአንድ ፎቅ ላይ የሚገኝ የ2ኛ ወለል ድግድጋ ተጋጭቶ ግማሽ ያክሉ ህንፃው ውስጥ ገብቶ ያመለክታል።

የባለስልጣኑ ቃል አቀባይ ካፕቴይን ስቴፈን ሆርነር፥ ተሽከርካሪው በከፍተኛ ፍጥነት በመጓዝ ላይ እያለ ከመንገድ አካፋይ ጋር በመጋጨቱ ነው ይህ አደጋ የደረሰው ይላሉ።

በወቅቱ አሽከርካሪው በትክክልኛ አቅጣጫ እያሽከረከረ አልነበረም ያሉት ቃል አቀባዩ፥ በዚህ ወቅት ተሽከርካሪው ከመንገድ አካፋይ ጋር በሚጋጭበት ጊዜ አየር ላይ ሳይንሳፈፍ አልቀረም ብለዋል።

አየር ላይ የተንሳፈፈው ተሽከርካሪም በአንድ የጥርስ ህክምና ክሊኒክ ሁለተኛ ወለል ጋር በመጋጨት እዛው ላይ ተንጠልጥሎ መቅረቱንም ሆርነር ያስረዳሉ።

በአደጋው ውቅት ሁለት ሰዎች ተሽከርካሪው ውስጥ ነበሩ ያሉት ሆርነር፥ አንደኛው ተሳፋሪ በራሱ ከተሽከርካሪው ሲወጣ፤ ሌላኛው ግን ለሰዓታት ታግቶ ከቆየ በኋላ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በከባድ መሳሪያዎች ተጠቅመው እንዳወጡት ተናግረዋል።

ሁለቱም ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን የሚናገሩት ሆርነር፤ በወቅቱም ሆስፒታል እንደወሰዷቸው አስታውቀዋል።

ሆርነር አደጋው በምን ምክንያት እንደተከሰተ መረጃ የለንም ቢሉም፤ ፖሊስ ግን አሽከርካሪው በወቅቱ ናርኮቲክስ የተባለ አደገኛ አደንዛዥ እፅ ወስዶ ነበር ብሏል።

ምንጭ፦ www.ndtv.com