ለህክምና የሚያስፈልገውን 500 ሺህ ብር ለመሰብሰብ አደባባይ የወጣው የሰበታው ነዋሪየ4 ሚሊየን ብር ሎተሪ እድለኛ ሆኗል

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባጋጠመው የልብ ህመም ምክንያት ወድ ውጭ ሄዶ ህክምናውን ለመከታተል ገንዘብ ሲሰበሰብለት የነበረው ግለሰብ የገና ስጦታ 1ኛ እጣ አሸናፊ ሆኗል።

ነዋሪነቱ በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ የሆነው አቶ አብዱልሀኪም አህመድ ነው በገና ስጦታ ሎተሪ 1ኛ ዕጣ 4 ሚሊየን ብር ዕድለኛ የሆነው።

የ43 ዓመቱ አቶ አብዱልሀኪም ልብስ በመስፋት ራሱንና ሁለት ልጆቹን ያስተዳድራል።

ሆኖም ግን ከ7 ወር በፊት ለልብ ህመም በመዳረጉ ስራውን ለማቆም የተገደደ ሲሆን፥ በቤተሰቦቹ እርዳታም ኑሮውን በመግፋት ላይ ነበር።

አቶ አብዱልሀኪም ባጋጠመው የልብ ህመም ምክንያት ህክምናውን ሲከታተል ቢቆይም፥ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሐኪሞች ቡድን ህንድ ወይም ታይላንድ ባንኮክ ሄዶ እንዲታከም ይወስናል።

ይህንን ተከትሎም ቤተሰቦቹና ወዳጅ ዘመዶቹ ለህክምናው የሚያስፈልገውን 500 ሺህ ብር የመታከሚያ ገንዘቡን እየሰበሰቡለት ቆይተዋል።

ሆኖም ግን ታህሳስ 29 2010 ዓ.ም የወጣው የገና ስጦታ ሎተሪ ለአቶ አብዱልሀኪም ያልተጠበቀ ደስታን ይዞለት መጥቷል።

ለመታከሚያው የሚያስፈልገውን 500 ሺህ ብር ለማሟላት ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ የነበረው አቶ አብዱልሀኪም በገዛው የገና ሎተሪ የ4 ሚሊየን ብር አሸናፊ መሆን ችሏል።

ዕድለኛው በዛሬው ዕለት እድለኛ መሆኑን እንዳረጋገጠም ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።