ተማሪዎች እስከ 736 የአሜሪካ ዶላር ከፍለው ዩኒፎርም እንዲያሰፉ የጠየቀው ትምህርት ቤት

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 6 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በጃፓን ቶኪዮ የሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከትምህርት ቤት ዩኒፎርም ጋር በተገናኘ ያሳለፈው ቀጭን ትዕዛዝ መነጋገሪያ አድርጎታል።

ትምህርት ቤቱ በቶኪዮ በምትገኘውና የፋሽን አካባቢ በሆነችው ጊንዛ በተሰኘች አካባቢ የሚገኝ ትምህርት ቤት ነው።

ታዲያ ከሰሞኑ ይኼው ትምህርት ቤት ተማሪዎቹ ለብሰው እንዲመጡ ያዘዘው ዩኒፎርም ለተማሪ የማይገባ አይነትና በዋጋውም እጅግ ውድ ስለመሆኑ ተነግሯል።

ታይሜይ የተሰኘው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፥ ተማሪዎቹ አርማኒ በተሰኘው የጣሊያን ኩባንያ የተዘጋጁ ዩኒፎርሞችን እንዲለብሱ ነው ያዘዘው።

የትምህርት ቤቱ ትዕዛዝ ተማሪዎቹ ሙሉ ዩኒፎርሞቹን ከ700 የአሜሪካ ዶላር በላይ በማውጣት እንዲገዙ ያስገድዳል።

ይህ መሆኑ ግን በተማሪ ወላጆች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሯል ነው የተባለው፤ የወላጆች ቅሬታም በሃገሪቱ ፓርላማ ለውይይት ቀርቧል።

ትምህር ቤቱ ሃሳቡን ያቀረበው ከዚህ ቀደም ተማሪዎች ይለብሱት የነበረውን ዩኒፎርም በአዲስና ዘመናዊ በሆነ መልኩ ለመቀየር በማሰብ ነው ተብሏል።

ይሁን እንጅ ለአንድ ሙሉ ዩኒፎርም ከ80 ሺህ የጃፓን የን በላይ ወይም እስከ 736 የአሜሪካ ዶላር ማውጣት እጅጉን ውድና አግባብ አይደለም በሚል ተቃውሞ አስተናግዷል።

የአሁኑ የትምህርት ቤቱ ውሳኔም የትምህርት ቤት ክፍያ አሳሳቢ ለሆነባቸው የአካባቢው ወላጆች ሌላ ጫና ይፈጥራል ነው የተባለው።

ከዚህ ቀደም በትምህርት ቤቱ መደበኛ የሚባል ዩኒፎርም እስከ 155 የአሜሪካ ዶላር ለወንዶች፥ ለሴቶች ደግሞ እስከ 176 የአሜሪካ ዶላር ይጠይቅ ነበር።

አዲሱ ዩኒፎርም ግን ከ310 የአሜሪካ ዶላር ጀምሮ እስከ 736 የአሜሪካ ዶላር ድረስ ዋጋ ይጠይቃል።

ይህ ደግሞ እጅጉን የበዛና አግባብ ያልሆነ ነው በሚል ወላጆች ተቃውሟቸውን በተለያየ መልኩ ለትምህርት ቤቱ አድርሰዋል።

ወላጆች አሁንም ተቃውሞ ቢያሰሙም ትምህርት ቤቱ ትክክለኛ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም አዲሱ ዩኒፎርም ከመጭው ሚያዚያ ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋልም ብሏል።

 

 

 

ምንጭ፦ odditycentral.com/