በቢሾፍቱ ሆስፒታል አንዲት እናት 4 ልጆችን በአንድ ጊዜ ተገላገለች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቢሾፍቱ ሆስፒታል አንዲት እናት አራት ልጆችን በአንድ ጊዜ መገላገሏ ተነግሯል።

እናት ወይዘሮ ሺብሬ አሰፋ ትባላለች፤ ከዚህ ቀደም ልጆች ለመውለድ ካላት ፍላጎት የተነሳ አራት ጊዜ ፀንሳ አልተሳካላትም ነበር።

ወይዘሮ ሺብሬ ነዋሪነቷ በምስራቅ ወለጋ ዞን ዲጋ ወረዳ አርጆ ጉደቱ ከተማ ነው።

4_mom_b.jpg

ሺብሬ ልጅ ለመውለድ ካላት ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ ለአምስተኛ ጊዜ ከፀነሰች በኋላ አስፈላጊውን የህከምና ክትትል በነቀምቴ ሆስፒታል በማድረግ ላይ ነበረች።

ሆኖም ግን ከዚህ ቀደም ካጋጠማት ነገር በመነሳት ስጋት ስለተፈጠረባት፤ ወደ አዲስ አበባ ቀረብ ብላ የተሻለ የህክምና ለማግኘት ዱከት ከተማ የሚኖረው ወንድሟ ጋር ሄደች።

ዱከም ከተማ ወንድሟ ቤት እንዳለች ምጥ የያዛት እናት ወይዘሮ ሺብሬ ወደ ቢሾፍቱ ሆስፒታልም ትወሰዳለች።

በመጨረሻም የቢሾፍቱ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች ባደረጉላት የቀዶ ጥገና ህክምና አራት ወንድ ልጆችን በአንድ ጊዜ በመገላገል፤ ልጅ ወልዶ የመሳም ፍላጎቷ እውን ሆኖላታል።

በቢሾፍቱ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያ ዶክተር ሰለሞን ወርቁ፥ በአንድ ጊዜ 4 እና ከዚያ በላይ የመውለድ አጋጣሚ ከ60 ሺህ ሴቶች በአንድ ሴት ላይ ሊያጋጥም ይችላል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አራቱም ህጻናት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ከቢሾፍቱ ከተማ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።