በስሙ ምክንያት በቀይ ካርድ ከሜዳ የተባረረው እግር ኳስ ተጫዋች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በእንግሊዝ ብሄራዊ ሊግ የሚወዳደር ክለብ ውስጥ የሚጫወተው የእግር ኳስ ተጫዋች በስሙ ምክንያት በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

ሳንቼዝ ዋት የተባለው የ27 ዓመቱ እግር ኳስ ተጫዋች ስሙን ለእለቱ ዳኛ በሚያስረዳበት ጊዜ ነው ካለመደማመጥ የተነሳ ከሜዳ ሊወጣ የቻለው።

ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው፥ የእንግሊዝ ብሄራዊ ሊግ ክለቡ ሀሜል ሀምፕስቲድ ታወን ክለብ ከኢስት ቶሩክ ጋር በሚጫወቱብት ጊዜ ሳንቼዝ ዋት ጥፋት ይሰራል።

ጨዋታውን ሲመሩ የነበሩት ዳኛ ዳን ሀልሜ ለዋት ሳንቼዝ ቢጫ ካርድ ያሳዩትና ስሙን ይጠይቁታል፤ ሳንቼዝ ዋትም “ዋት” በማለት ስሙን ይነግራቸዋል።

ዳኛውም ተጫዋቹ “ኋት” ወይም በአማርኛ ትርጉሙ “ምን” ያለ ይመስላቸውና በድጋሚ ስሙን ይጠይቁታል።

እግር ኳስ ተጫዋቹም በድጋሚ “ዋት” በማለት ይልመልስላቸዋል፤ ዳኛው በተደጋጋሚ ሲጠይቁት የተጨዋቹ መልስም ተመሳሳይ ይሆናል።

ታዲያ ስሙን እየነገረኝ አይደለም አውቆ እየቀለደ ነው በሚል የተረዱት ዳኛው ተጫዋቹን በቀይ ካርድ ከሜዳ ማስወጣታቸው ነው የተነገረው።

የሀሜል ሀምፕስቲድ ታወን የእግር ኳስ ክለብ ዳይሬክተር ዴቭ ቦጊንስ፥ “እንዲህ አይነቱ ስህተት በሰዎች ዘንድ መፈጠሩ አይቀሬ ነው፤ ዳኛውን ጨምሮ ሁሉም ሰው የተፈጠረውን ሲረዱ በእጅጉ ተገርመዋል” ብለዋል።

ዳኛው ከጨዋታው በኋላ ወደ ቦርድ መሰብሰቢያ ክፍል በመምጣት የተፈጠረውን ነገር ከተረዱ በኋላ ይቅርታ ጠይቀዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፥ ስህተቱ እንዴት እንደተፈጠረም ማብራሪያ ሰጥተዋል ብለዋል።

በስሙ ምክንያት በቀይ ካርድ ከሜዳ የተባረረው ሳንቼዝ ዋት ለተየያዩ ሀያል የእግር ኳስ ክለቦች ተጫውቷል።

ዋት በ18 ዓመቱ ለአርሰናል ተሰልፎ ሶሰት ጨዋታዎችን ማድረግ የቻለ ሲሆን፥ በአውሮፓውያኑ በ2009 በኢሚሬትስ ስታዲየም በተካሄደው የእንግሊዝ ሊግ ካብ ለአርሰናል ተሰልፎ ዌስት ብሮም ላይ ግብ አስቆጥሯል።

በተጨማሪም በብሄራዊ ሊግ ውስጥ ላሉ እንደ ሊድስ ዩናይተድ እና ሼፍልድ ዩናይድት ክለቦች የተጫወተ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅትም በሀሜል ከተማ የእግር ኳስ ክለብ ውስጥ በውሰት እየተጫወተ ይገኛል።

 

ምንጭ፦ www.bbc.com