ብላክ ፓንተር ፊልም በአንድ ወር ውስጥ 1 ቢሊየን ዶላር አስገባ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በርካታ ጥቁር ተዋናያን የተሳተፉበት ብላክ ፓንተር ፊልም ለእይታ በበቃባቸው ሀገራት 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማድረጉ ተነገረ።

ፊልሙ በቴክኖሎጂ እጅግ የዘመነች እና ዋካንዳ በተባለች ምናባዊት አፍሪካዊ ሀገር ላይ ተመስርቶ የተሰራ ፊልም ነው።

በዚህም በማርቭል የፊልም ተቋም ከተሰሩት ፊልሞች መካከል ከፍተኛ ገቢ ያስገባ መሆኑ ነው የተነገረው።

ከረጂም ጊዜያት በኋላ ለአራት ተከታታይ ሳምንታት በቀዳሚነት የቆየው ብላክ ፓንተር ፊልም፥ በቻይና ብዙ ተመልካቾችን በመሳቡ ገቢው ከፍ ማለቱ ተገልጿል።

በጥቁሩ ዳይሬክተር ራየን ኩግለር ዳይሬክት የተደረገው ብላክ ፓንተር ፊልም፥ በርካታ ጥቁር ተዋንያን የተሳተፉበት በመሆኑም የበርካቶችን ትኩረት መሳቡ ተነግሯል።

በተጨማሪም የጥቁሮች ፊልም በአለም ላይ ትኩረት አያገኝም ብለው ለሚያስቡ ግዙፍ የፊልም ኢንዳስትሪዎች አመለካከታቸውን እንዲያስተካክሉ የሚያስገድድ ፊልም እንደሆነ ተጠቁሟል።

ብላክ ፓንተር ከተጠበቀው በሁለት እጥፍ ገቢ እንዳገኘም ነው የተገለፀው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ እና rottentomatoes.com