ባለቤቱን ከፍቅረኛዋ ጋር ያጋባው ህንዳዊ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) አንዳንድ ጊዜ ያልተለመዱና ምናልባትም ሊሆኑ አይችሉም የሚባሉ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ይስተዋላል።

ከሰሞኑ ከወደ ህንድ የተሰማው ዜና ደግሞ አነጋጋሪም አስገራሚም ሆኗል፤ ባል በትዳር የተጣመረችው የህይዎት አጋሩ ፍቅረኛየ ካለችው ወጣት ጋር በትዳር እንድትጣመር ፈቅዶላታል።

ነገሩ እንዲህ ነው በህንድ ኦዲሻ ግዛት ነዋሪ የሆነው የ28 አመቱ ባሱዴፕ ታፖ ከ24 አመቷ ወጣት ጋር በሚኖርበት ማህበረሰብ ባህልና ወግ መሰረት በጋብቻ ይጣመራል።

ከጋብቻ በኋላ የቤተሰብና የአካባቢውን ማህበረሰብ ምርቃት ተቀብለው ወደ ጎጇቸው ያመራሉ።

ከተጋቡ ከስድስት ቀናት በኋላ ግን ወደ አዲሶቹ ሙሽሮች መኖሪያ ቤት ሶስት ወጣት ወንዶች ለጥየቃ ይመጣሉ።

ከመጡት መካከልም አንደኛውና የአዲሷ ሙሽራ የአጎት/አክስት ልጅ እንደሆነ የተነገረለት ወጣት ቤቱ ውስጥ ሲቀር፥ ሁለቱ ጓደኞቹ ደግሞ ሰፈሩን ለመጎብኘት በሚል ከቤት በመውጣት ወዲያ ወዲህ ማለት ይጀምራሉ።

ይህን ሁኔታ ያስተዋሉት የሙሽሮቹ ጎረቤቶች ታዲያ፥ አዲስ ሙሽራ ምን ሲባል ባለቤቷ ካልሆነ ወንድ ጋር ቤት ውስጥ ትቀመጣለች በሚል ወደ ቤቱ ዘው ብለው ይገባሉ።

ዚያም የስጋ ዘመድ እንደሆነ የተነገረለትን ወጣት፥ ከአዲስ ሙሽራ ጋር ባዶ ቤት መቀመጥ የለብህም በማለት እየጎተቱና እየደበደቡ ከጥንዶቹ ቤት ያስወጡታል።

ይህን በቅርብ ርቀት ሆና ትከታተል የነበረችው አዲስ ሙሽራም፥ የስጋ ዘመድ የተባለው ወጣት የልጅነት ፍቅረኛየ ነው በማለት እውነቱን ትናገራለች።

ከልጅነት እስከ እውቀት ተዋደውና ተፋቅረው ቢቆዩም በእርሷ ቤተሰቦች እምቢታ ምክንያት፥ የፈለገችው በጋብቻ የመጣመር ሃሳብ አለመሳካቱንም ለአካባቢው ነዋሪዎች ታስረዳለች።

በዚህ ምክንያት ቤተሰቦቿ ጥያቄዋን ገፍተው ለታፖ እንደደሯትና እነርሱም ፍቅራቸውን በድብቅ ይገልጹ እንደነበርም ገልጻለች።

መሰል ሁኔታዎች በአጋጣሚ ሊከሰቱ ቢችልም በህንድ ግን እንዲህ አይነት ሁኔታ መዘዙ የከፋ ነው፤ ማመንዘር በህንዳውያን ለከፋ ቅጣት ይዳርጋልና።

አዲሱ ሙሽራ ባሱዴፕ ታፖ ግን ይህን ሁኔታ ከሰማ በኋላ አጸፋውን በተቃራኒው ነበር የመለሰው፤ ለሁሉም ይበጃል ያለውን ሰላማዊ ማስታረቂያ ሃሳብ በማቅረብ።

“ነገሩ እንዲህ ከሆነ ባለቤቴ ፍቅረኛዋን ማግባት ትችላለች ይህም ለሁላችን ይበጃል” ነበር ያለው ታፖ።

ለዚህም ቤተሰቦቿን አግኝቶ ካነጋገረና እርሱ ባቀረበው ሃሳብ እንዲስማሙ ጠይቆ ካግባባቸው በኋላ ለባለቤቱና ለፍቅረኛዋ ሌላ ሰርግ ሰርገዋል።

“ይህን መፍትሄ ባላቀርብ ኖሮ የሶስት ሰዎች ህይዎት ይጠፋ ነበር” ያለው ሙሽራው ታፖ፥ “ውሳኔው ብቸኛው የመፍትሄ ሃሳብና ሁሉንም ደስተኛ” የሚያደርግ መሆኑን ተናግሯል።

የሙሽራውን ወላጅ እናት ጨምሮ የአካባቢው ገዥና ማህበረሰብ የታፖን ሃሳብ በማድነቅ የባለቤቱን ሁለተኛ ሰርግ በደስታ ተቀብለውታል።

ሰርጉ በሰላም የተሰረገ ሲሆን፥ በሳምንት ውስጥ ሁለት ጊዜ የተሞሸረችው ወጣትና ሁለት ባሎቿም ውሳኔውን በፀጋ ተቀብለዋል ነው የተባለው።

 

ምንጭ፦ ኦዲቲ ሴንትራል