በደቡብ ካስቴል ዋንጫ ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ዲቻ አቻ ሲለያዩ ሃዋሳ ከተማ አሸንፏል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከተጀመረ ሶስተኛ ቀኑን የያዘው የደቡብ ክልል ካስቴል ዋንጫ ዛሬ የምድብ ሀ ጨዋታዎችን አስተናግዷል።

8 ሰዓት ላይ የምድቡ መሪ ፋሲል ከነማ ከወላይታ ዲቻ ተጫውተው አንድ አቻ ተጠናቋል።

በጨዋታው ፋሲል ከነማዎች ከዕረፍት በፊት በክሪስቶፈር አሞስ ኦቢ ባስቆጠሩት ጎል አንድ ለዜሮ መምራት ችለው ነበር።

ከእረፍት መልስ ወላይታ ዲቻዎች ጃኮ አራፋት ባስቆጠረው የፍጹም ቅጣት ምት ጎል አቻ መሆን ችለዋል፤ ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።

በሁለተኛው የምድቡ ጨዋታ ደግሞ ሃዋሳ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 2 ለ 0 አሸንፏል፤ ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ቡና ከውድድሩ ውጭ ሆኗል።

ምድቡን ፋሲል ከነማና ወላይታ ዲቻ በእኩል አራት ነጥብ ይመሩታል።

ትናንት በተደረጉ የምድብ ለ ጨዋታዎች፥ አርባ ምንጭ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 0 ለ 0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሲዳማ ቡና ደግሞ ወልዲያ ከተማን፥ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።