በፕሪሚየር ሊጉ አርሰናል ዌስት ብሮምን 2 ለ 0 አሸንፏል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ትናንት ምሽት በተካሄደ አንድ ጨዋታ አርሰናል ዌስት ብሮምን 2 ለ 0 አሸንፏል።

በኢምሬትስ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ለመድፈኞቹ የማሸነፊያ ሁለቱን ግቦች ፈረንሳዊው አሌክሳንደር ላካዜቲ ከመረብ አዋህዷል።

ላካዜቲ በክረምት የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በክለቡ ሪከርድ በሆነ ዋጋ ከሊዮን መምጣቱ ይታወሳል።

ተጫዋቹ በመድፈኞቹ ማሊያ በኢምሬትስ ስታዲየም በተሰለፈባቸው የመጀመሪያ ሶስት የፕሪሚየርሊግ ጨዋታዎች ግብ በማስቆጠር ከ1988 ወዲህ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል።

የትናንቱ ውጤት አርሰናልን በ10 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል።

መድፈኞቹ ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ ያላቸው የነጥብ ልዩነት ስድስት ሲሆን፥ አራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቶተንሃም ጋር ደግሞ በአንድ ነጥብ ብቻ ይራራቃሉ።

በምሽቱ ጨዋታ የዌስት ብሮሙ ጋሪዝ ባሪ በ633 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ አዲስ ክብረወስን በስሙ አስመዝግቧል።

የ36 ዓመቱ ባሪ በቀድሞው የማንቸስተር ዩናትድ የክንፍ ተጫዋች ሪያን ጊግስ ተይዞ የነበረውን በ632 ጨዋታዎች የመሰለፍ ክብረወሰን በአንድ ጨዋታ በመብለጥ ቀዳሚው ሆኗል።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች መጠናቀቃቸውን ተከትሎ፥ ማንቸስተር ሲቲ በ16 ነጥብ እና በ19 ንፁህ ግብ አንደኛ ሆኖ ይመራል።

የሆዜ ሞውሪንሆው ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው።

ቼልሲ በአንቶኒዮ ኮንቴ እየተመራ በስድስት ጨዋታዎች 13 ነጥብ በመሰብሰብ ሶስተኛ ላይ ይገኛል።

ቶተንሃም ሆትስፐርስ፣ ሊቨርፑል እና ዋትፎርድ በተመሳሳይ 11 ነጥብ በመያዝ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በሊጉ የግርጌ ሰንጠረዥ ደግሞ ዌስትሃም ዩናይትድ በአራት ነጥብ 18ኛ፣ ቦርንማውዝ በሶስት ነጥብ 19ኛ እንዲሁም ስድስቱንም ጨዋታዎች የተሸነፈው ክሪስታል ፓላስ ያለምንም ነጥብ 20 ደረጃ ላይ ይገኛሉ።